በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የኢፌዲሪ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ ባለው የዓለም የመንግስታት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በዛሬው የመርሀ ግብሩ መክፈቻ ላይም መንግስታዊ የአስተዳደር አቅምን በሚያዳብሩ ዓለም አቀፋዊ ስጋቶች እና እድሎች ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ በልዑካን ቡድኑ በመወከል ተሳትፎ ማድረጓ ተጠቅሷል።
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ውጤታማ ፖሊሲ ማውጣት፣ የዜጎች ተሳትፎ፣ ዘላቂ ልማት፣ የውኃና መስኖ አጠቃቀም እና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎች የመድረኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ ተመላክቷል።
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑክ በከፍተኛ ደረጃ በሁለትዮሽና ባለ ብዙ ወገን መድረኮች፣ በፓናል ውይይቶች እንዲሁም የጎንዮሽ መስተጋብራዊ ተሳትፎ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
ልዑካኑ በጉባዔው ለመሳተፍ ዱባይ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) እና ዲፕሎማቶች አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተጠቁሟል።