በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተከናወኑ ተግባራት በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊው እና በፖለቲካው ዘርፍ አበረታች ውጤቶች በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው የክልሉ የ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የአፈጻጻም ሪፖርት በርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ቀርቧል።
በሪፖርቱ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና ልማት ስራዎች ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለአርሶ አደሩ 145 ሺህ 909 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ መሰራጨቱም ተገልጿል።
በክልሉ በ5 ሚሊዮን ኮደርስ 11 ሺህ 20 ሰልጣኖች ተመዝግበው በመማር ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
በመደበኛና ማዘጋጃቤታዊ ገቢ በግማሽ ዓመቱ 5 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተጠቅሷል።
በክልሉ 54 አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ፕሮጀክቶች ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል መመዝገቡም ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት በክልሉ በመሰረተ ልማት በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉም ተብሏል።
በክልሉ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማስጠበቅ እንዲሁም በአፈፃፀም ሂደት ውስጥ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር አስገንዝበዋል።
የክልሉ ህዝብ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተደራጀ መልኩ ከመመለስ ባሻገር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባሕል ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።