38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን እንደሚሰጡት ይጠበቃል

3 Days Ago 225
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን እንደሚሰጡት ይጠበቃል

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ከአንድ ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን የሰጡታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከየካቲት 8 እስከ 9 2017 ዓ.ም የሕብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአፍሪካ ህብረት ብሄራዊ የጉባዔ አመቻች ኮሚቴ አባል በመሆን ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ከነዚህም መካከል ስብሰባውን ለሚዘግቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች “ፕሬስ ፓስ" እንዲያገኙ ማድረግ፤ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አካላት የመዳረሻ ቪዛ የማመቻቸት እና ለሙያ መገልገያ መሳሪያዎቻቸው የከስተም ክሊራንስ ስራዎችን መስራት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

እነዚህን ስራዎች ቀልጣፋ ለማድረግ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ጉምሩክ፤ በአፍሪካ ህብረት ባጅ ሴንተር እንዲሁም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት በቂ የሰው ኃይል በመመደብ የተቀላጠፈ የ24 ስዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ነው ባለስልጣኑ የገለጸው።

በዚህ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ እስካሁን 390 የሀገር ውስጥ እና 530 የውጭ ጋዜጠኞች መመዝገባቸው ባለስልጣኑ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል።

በዚህ ሂደት ሚዲያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻልና የእንግዳ ተቀባይነታችንን በማረጋገጥ ስብሰባው መልካም ገፅታን አጉልቶ በማሳየት ይጠናቀቅ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top