“አትሌቲክስ አፍቃሪው ብቻ ሳይሆን አትሌቶችም ጭንቀት ላይ ነው ያሉት” - የስፖርት ጋዜጠኞች

2 Mons Ago 725
“አትሌቲክስ አፍቃሪው ብቻ ሳይሆን አትሌቶችም ጭንቀት ላይ ነው ያሉት” - የስፖርት ጋዜጠኞች

በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በምትጠበቅባቸው ርቀቶች ውጤት አለማምጣቷ፤ በውድደሩ ውስጥ ውዝግቦች መኖራቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወዴት እየሄደ ነው የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ችሏል። 

የፓሪስ ኦሎምፒክ ውጤት ማጣትን በተመለከተ የስፖርት ጋዜጠኞች በኢቢሲ ዳጉ መሰናዶ ላይ ውይይት አካሂደዋል። 

በኢቢሲ ስፖርት ክፍል የስፖርት ጉዳዮች አርታኢና የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው ንዋይ ይመር፥ አሁን ላይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በሚመለከታቸው አካላት መካከል ያለው ውዝግብ አትሌቲክሱን እየጎዳው ነው፤ ለዚህም ማሳያው ለፍተው ውጤት ባመጡ አትሌቶች መደሰትና ማክበር ጭምር አለመቻላችን ነው ብሏል። 

የሱፐር ስፖርት የአትሌቲክስ ተንታኙ ኃይለእግዚአብሄር አድሃኖም በበኩሉ፥ የፓሪስ ኦሎምፒክ የሁሉም ውጤት ማጣታችን ችግሮቻችን መጨረሻው ሊሆን ይገባል ብሎ፤ ከ1968 ጀምሮ ሜዳሊያ ውስጥ ከገባንበት የትራክ ውድድር ውጭ ሁነናል፣ በዚህም ልንቆጭ ይገባናል ሲል ገልጿል። 

ለዚህ የዳረጉን ባለፉት ኦሎምፒኮች ተከታትለው የመጡ ችግሮች፥ ተቀናጅቶ መስራት አለመቻል፣ ቆሞ የቀረ የስልጠና እና የታክቲክ ችግር፣ ድሮ በምናሰለጥንበት ተመሳሳይ መንገድ መሄድ፣ ተስማምቶና ተግባብቶ ያለመስራት፣ ለአትሌቶች ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር፣ ለባለሞያዎች ነፃነት አለመስጠት መሆናቸውንም ጠቁሟል። 

በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የስፖርት ክፍል ምክትል አዘጋጁ ሁሴን ግዛው በበኩሉ፥ ጎበዝ አትሌቶች ቢኖሩም የአሰራሩ ሂደቱ የሽንፈት ስነልቦና እንዲኖር አድርጓል ብሏል። 

ለዚህም በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ የነበረውን የአትሌቶች ስሜት መመልከት በቂ መሆኑን ተናግሯል። 

በኢቢሲ ስፖርት ዲፓርትመንት ዋና አዘጋጅ የሆነውና በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ወደ ፓሪስ አቅንቶ የነበረው ግርማ በቀለ፥ ድልን ለመዘገብ ጓጉቼ ብሄድም እዛ ያለው ወጤት ግን የኔንና የባልደረቦቼን ቅስም የሰበረ ነበር ሲል ገልጾታል። 

ጋዜጠኞቹ አክለውም የዘንድሮው ኦሎምፒክ ዲፕሎማሲያችን ላይም ብዙ ችግሮችን ያመጣ ነው ብለውታል። 

በዚህም የተነሳ የአሸናፊነት ስነልቦና እና የአንድነት ስሜት አጥተናል፤ ኢትዮጵያውያን በውድድሩ አሉበት ሲባል የነበረን ሞገስ ጠፍቷል፤ ይህ ትልቅ ውድቀትና ለአትሌቶችም የስነልቦና ፈተና ነበረ ሲሉ ተናግረዋል። 

ፓሪስ የነበረው ውዝግብም ውጤታችን ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው። ጋዜጣዊ መግለጫ አለመኖሩ፣ ግልፅ የሆነ አሰራር አለመቀመጡ ስህትት ነበር ሲሉም ትዝብታቸውን አጋርተዋል። 

ፌዴሬሽኑ ለዘገባ ለሚሄዱ ጋዜጠኞች የሚሰጠው ፍቃድ በኦሎምፒክ ኮሚቴውና በፌዴሬሽኑ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነበር፤ ይህ ደግሞ መረጃዎች ፍትሃዊ እንዳይሆኑና ወገንገኝነት እንዲታይባቸው አድርጓል ነው ያሉት። 

ከዚህ በተጨማሪ በቦታው የነበሩት የፕሬስ አታሼ ሲፈለጉ አለመገኘታቸው ችግር ፈጥሯል የሚል ቅሬታም አንስተዋል። 

በቀጣይ የአትሌቲክሱን ዘርፍ ለማሻሻል መደማመጥ ያስፈልጋል ያሉት ጋዜጠኞቹ፤ ብዙ ክብረ ወሰን የያዙ አትሌቶች አሉን፣ አስተዳደራዊ ችግሮች ከተፈቱ ውጤት ማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም፤ ይህ የሚሆነው ግን አመራሮቹ ከእልኸኝነት ወጥተው መነጋገር  ሲችሉ ብቻ ብቻ ነው ብለዋል። 

ከዚህ ባለፈ በቀን ሁለቴ ልምምድ የሚሰሩና ለማራቶን በሳምንት 200 ኪሎ ሜትር እየሮጡ ለሀገራቸው ድል የሚታገሉ አትሌቶቻችን ዛሬ ላይ ፍርሃት ውስጥ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል። 

በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ቀርቶ በግል ውድድር ለማድረግ አትሌቶቻችን ተሳቀው ነው ሚገኙት፤ ይህ የሆነው በአመራሮች ምክንያት ነው፤ ለዚህም መፍትሄ ያስፈልገዋል ሲሉ ጠይቀዋል። 

የትራክ ተወዳዳሪዎች ፓሪስ ለመሄድ አንድ ሳምንት እስኪቀራቸው መመረጣቸውን አያውቁም ነበር፤ ያም ለስነልቦና ጉዳት ዳርጓቸዋል የሚሉት ጋዜጠኞቹ፤ አትሌቲክሱ ችግር ላይ መሆኑን ሁሉም እየተናገረ ባለበት፥ "አይደለም፣ ትናንት እንደዚህ ዓይነት ውጤት አምጥትናል" እያለ የሚክድ አመራር ባለበት ለውጥ ይመጣል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አልሸሸጉም። 

"ህዝብ ስለተናገረ አይመለከተኝም፤ እኔን የሚመርጠኝ ጠቅላላ ጉባኤ ነው" የሚል አካሄድ አዋጪ አይደለም፤ የሚሰራው ለህዝብ መሆኑ ይታወቅ፤ መንግሥትም ቢሆን አትሌቲክሱን እንደ ትልቅ ጉዳይ ሊመለከተው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። 

ከሰሞነኛ ወሬ እና ውይይት ያለፈ ሪፎርም እና መሰረታዊ የአሰራር ለውጥ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ያስፈልጋል ብለው እንደሚያምኑም በውይይታቸው ወቅት ገልፀዋል። 

ህዝቡም በውድድሩ ብዙ የለፉትንና ውጤት ለማምጣት የታገሉትን አትሌቶች  ሞራል ሊጠብቅ እንደሚገባ የገለፁት ጋዜጠኞቹ፤ ሁሉም ዘርፉ እየሞተ እንደሆነ በመረዳት ለመታደግ ሊሰራ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በናርዶስ አዳነ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top