በአንካራ በተካሄደው ድርድር ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ ማድረግ ተችሏል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

2 Mons Ago 301
በአንካራ በተካሄደው ድርድር ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ ማድረግ ተችሏል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በአንካራ በተካሄደው ድርድር ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተረዳበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

መንግስት ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር በጋራ የማልማት እና የመጠቀም እንቅስቃሴውን እንደሚገፋበት ተነግሯል፡፡

ይህ የተገለፀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ነው፡፡

በሳምንታዊ መግለጫውም በቱርክ አንካራ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የተደረገው ሁለተኛው ዙር የሁለትዮሽ ድርድር ተስፋ ሰጭ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና ልዑካቸው በአንካራው የሁለትዮሽ ድርድር ተሳትፎ አድርገው ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ፍላጎት ግልጽ በሆነ መልኩ ማስረዳታቸውንም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ በሶስተኛው ዙር ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ ፈቃደኛ እና ዝግጁ መሆኗም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ቃል አቀባዩ በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚደረገው የኃይል ሥምሪት በቀጣናው ላይ አዲስ ውጥረት በመፍጠር በሰላም እና መረጋጋት ላይ አደጋ ሊፈጥር በማይችል መልኩ በጥንቃቄ ሊዋቀር እንደሚገባ ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነት አደጋ የሚጋርጥ ጉዳይ ከተስተዋለ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ራሷን የመከላከል መብቷን ታረጋግጣለችም ብለዋል ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፡፡

በሌላ በኩል በሊባኖስ ያለው ቀውስ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ በዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ንብረት ለመታደግ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩንም ቤሩት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመሆን በትኩረት እየተከታተለው ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የከፋ ነገር እንኳን ቢመጣ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባም አምባሳደር ነብዩ ተድላ አሳስበዋል፡፡

በሳምንታዊ መግለጫውም ኢትዮጵያ በሳምንቱ ያከናወነቻቸው ዓበይት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችም ተመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ፍስሃ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top