በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ያልተገባ አለባበስ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ ደንብ ወጣ

10 Mons Ago 821
በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ያልተገባ አለባበስ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ ደንብ ወጣ

በሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች የአለባበስ ሥነ-ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። 

ቢሮው በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣ ጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ደንብ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲስ ረቂቅ ደንብ አውጥቷል። 

አዲሱ ረቂቅ ደንብ በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አለባበስ፣ የፀጉር አያያዝ፣ በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ የሚደረጉ ጌጣ ጌጦች አጠቃቀምን እና የሚጠቀሟቸው ሽቶዎች መጠንን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል። 

ኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ይህንኑ ደንብ በተመለከተ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት አገልግሎቶች እና ብቃት ማረጋገጥ ደረጃ ምደባ ዳይሬክተሮት ዳይሬክተር ከሆኑት ወ/ሮ ገነት ይመር ጋር ቆይታ አድርጓል። 

ወ/ሮ ገነት በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሐሳብ፣ የማኅበረሰቡ አካል እንደመሆናችን በዕለት ተዕለት እቅስቃሴያችን ውስጥ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለውን የሠራተኞች ያልተገባ አለባበስ አስተውለናል፤ ጉዳዩ ከምልከታችን በተጨማሪ የማኅበረሰቡ ቅሬታ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

በዚህም በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የተራቆተ እና ሰውነታቸውን ከልክ በላይ የሚያሳይ ልብስ መልበስ እንደየማይችሉ ደንቡ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል። 

የሚታይ የሰውነት አካል ላይ ያለ ንቅሳት በአግባቡ መሸፈን እንዳለበት እና ሊታይ እንደማይገባውም በደንቡ መቀመጡን ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል ሽታው ከበድ ያለ ሽቶ መቀባት፣ ‘ሂዩማን ሄር’ ማድረግ፣ ከሸሚዝ በላይ የሚደረግ የአንገት ጌጥ እንዲሁም በጆሮ ላይ የተደረደሩ ጌጦች ማድረግ የማይቻል ሲሆን፤ ወንዶች በፍፁም የጆሮ ጌጥ ማድረግ እንደማይችሉ በረቂቅ ደንቡ ተደንግጓል። 

ይህ ረቂቅ ደንብ የመስተንግዶ ሥራ ላይ ብቻ እንደማያተኩር እና ለሁሉም የሥራ ዘርፍ የሚሆን የአለባበስ ሥርዓትን ያካተተ መሆኑን አንሥተዋል። 

ለአብነትም በላውንደሪ ቤቶች የማያንሸራትቱ መጫሚያዎች፣ በምግብ ማብሰያ ቦታዎች ከሚፈናጠሩ እና ከሚያቃጥሉ ነገሮች ሊከላከሉ የሚችሉ አልባሳት እና ሌሎችም ከተለያዩ የሥራ ዘርፎች ጋር የሚጣጣሙ እና ለሠራተኛው ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ረቂቅ ደንብ መሆኑን አክለዋል። 

ይህ ረቂቅ ደንብ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ቅድሚያ ለሠራተኛ ደኅንነት ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በተጨማሪም ማንኛውም ተገልጋይ ለባለድርጅቶቹ እና ለሠራተኞቹ ክብር እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ብለዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ያላቸው ባህል፣ ሥርዓት እና እሴት እንዳይሸረሸር የሚያደርግ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

በአፎሚያ ክበበው


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top