"ፈተናዎችን በመደመር መንገድ በትብብር፣ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከርና አሰባሳቢ ትርክት በመፍጠር መሻገር ይገባል"

10 Mons Ago 956
"ፈተናዎችን በመደመር መንገድ በትብብር፣ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከርና አሰባሳቢ ትርክት በመፍጠር መሻገር ይገባል"

የመደመር ጉዞ ላይ ያተኮረ ውይይት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካና የአስተዳደር መቀመጫ በሆነችው ቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው። 

"የመደመር ትሩፋቶች ለተሻለ ነገ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መድረክ የመደመር ጽንስ ሃሳብ ለሃገራዊ ብልፅግና በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የብልፅግና ፅ/ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ አረጋ፥ የመደመር ዓላማ መልካም የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ የተሰሩ ስህተቶችን ማረም እንዲሁም የመጻኢውን ትውልድ እድል የተሻለ ለማድረግ መሰረት መጣል ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል። 

ባለፉት ዓመታት ከመደመር መንገድ የተገኙ ትሩፋቶች፣ እድሎች እንዲሁም ያልተሻገርናቸውና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፥ በሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ያሉ ግጭቶች፣ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት የመሰሉ ችግሮችን በአግባቡ ልናስተዳድራቸውና ልንሻገራቸው ይገባል ብለዋል። 

ለዚህም በመደመር መንገድ በትብብር፣ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር እንዲሁም ሁሉን አሰባሳቢ ትርክት በመፍጠር ፈተናዎችን ልንሻገር ይገባል ብለዋል።

 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከመደመር መንገድ ተጠቃሚ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ባጋሩት መነሻ ፅሁፍ የጠቆሙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ፤ መሰረታዊ የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ለሌሎች በክልሉ ላገኘናቸው የመደመር ትሩፋቶች መሰረት የጣለ ነው ብለዋል። 

መደመርን መሰረት አድርገው በቀረቡት የመነሻ ፅሁፎች ላይም ውይይት ተደርጎባቸዋል። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀው መድረክ ላይ የፌደራልና የክልል መንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

በኮሰን ብርሃኑ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top