የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰማሩና በፓርኮቹ ያሉ አምራቾች ተጨማሪ ገበያ እንዲያገኙ ለመስራት ከስምምነት ተደረሰ

1 Yr Ago 707
የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰማሩና በፓርኮቹ ያሉ አምራቾች ተጨማሪ ገበያ እንዲያገኙ ለመስራት ከስምምነት ተደረሰ

የብራዚል አምራች ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾች በብራዚል ተጨማሪ የገበያ መዳረሻዎችን እንዲያገኙ ለመስራት ከስምምነት ተደርሷል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ከሆኑት ጃንዲር ፌሬራ ዶሳንቶስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ብራዚል በዘርፈ ብዙ መስኮች ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ግንኙነታቸውን በኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮችም ማጠናከር በሚቻልባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህም የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲያመርቱ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በብራዚል ገበያ መሸጥ እንዲችሉና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ለማስቻል ከስምምነት ደርሰዋል።

በማኑፋክቸሪንግ በተለይም በአግሮፕሮሰሲግ ዘርፍ ብራዚል ያላትን ረጅም ልምድና ተሞክሮ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር ወዳሉ ኢንቨስትመንቶች ማስፋፋት በሚቻልባቸው እና ተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ዉይይት አካሂደዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አምባሳደሩ አሁን ላይ በኮርፖሬሽኑ በኩል ያሉ እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፤ በተለይም ኢትዮጵያ በአግሮፕሮሰሲግ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንቨስትመንቶች በብራዚል ያለውን ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በቀጣይም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቢዝነስ ፎረም በጋራ እንደሚሰናዳ ተጠቁሟል።

ብራዚል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፣ በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በአለም 10ኛ እንዲሁም በመግዛት አቅሟ ደግሞ 8ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ የሚገኝ መካከለኛና ቅይጥ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ናት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ጋር በቅርቡ ተገናኝተው በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል ግንኙነትን ስለማጠናከር እና በብዝኃ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top