በሽግግር ፍትሕ ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

5 Mons Ago
በሽግግር ፍትሕ ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

ለሽግግር ፍትሕ ሂደት ስኬታማነት የሚያግዙ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስፋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በየትኛውም መልኩ የሚከሰት ግጭት እና አለመግባባት ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት የመጋለጥ ዕድላቸውን ያሰፋል።

በዚህም አለመግባባቶች የሚከሰቱባቸውን ጉዳዮች በመለየት መፍትሔን ማበጀት እና ማመላከት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕን በማካሄድ የተፈጠሩ ስህተቶችን ማረምን ጨምሮ ስጋቶችንም ማሻሻል የግድ አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ገልጸዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግ እንደ አገር የሽግግር ፍትሕ እንዲካሄድ ምክረ-ሐሳብ ካቀረቡ ተቋማት እና አካላት መካከል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አንዱ እና ዋነኛው ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊ እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ለማስቻል በቅድሚያ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነቱ፣ የአፈጻጸም ሂደቱ እና ፋይዳውን በሚመለከት የማኅበረሰብ ውይይቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ለሽግግር ፍትሕ አጋዥ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም በውይይቱ  ከተመላከቱ  ምክረ-ሐሳቦች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ የሽግግር ፍትሕን በሚመለከት እየተዘጋጀ ላለው ፖሊሲ ኮሚሽኑ በግብዓትነት አቅርቦታል ብለዋል።

በቀጣይም ፖሊሲውን በማውጣት እና በማዘጋጀት እየተሳተፉ ያሉ አካላት የጉዳዩን አስፈላጊነት በመገንዘብ በግብዓትነት የተገኙ ምክረ-ሐሳቦችን ማካተት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top