እስከ ታላቅ ባለሀብትነት ያደረሰ ‘የይቻላል እና የፅናት ተምሳሌትነት’ - ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

1 Yr Ago
እስከ ታላቅ ባለሀብትነት ያደረሰ ‘የይቻላል እና የፅናት ተምሳሌትነት’ - ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት አሁን ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ የሆኑ ታላቅ ልዕለ ሰብ የስፖርት ሰው ስለመሆኑ በርካቶች ይመሰክሩለታል፤የይቻላል መንፈስ ባለቤት መቻልን በቃል ሳይሆን በድርጊት የሚኖር ብርቱ ሰው ነውም ይሉታል። ከሌላ ዓለም የመጣ ፍጡር እስኪመስል ድረስ የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ብቃት እና ጀግንነት ከአጽናፍ አጽናፍ የናኘ ነው።
 
ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን አሸናፊነትን ክብረወሰንን በማሻሻል ያጀበው ብርቅዬው አትሌት 27 ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ጀግንነቱን አስመስክሯል።
ሚያዚያ 10 ቀን 1966 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል አርሲ- አሰላ የተወለደው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ፣ሀገሩን በዓለም መድረክ ከፍ አድርጓል። ለሀገሩ ክብር እና ኩራት ሕይወቱን ገብሯል። ላቡን እና እንባውንም አፍስሷል። ኢትዮጵያ የሰላም አየር ሲርቃትም ለሽምግልና ተሰልፏል።
 
በተለያዩ ርቀቶች ለረጅም የውድድር ዘመናት በመሮጥ ቀዳሚ የሚሆነው ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ለ28 ዓመታት በቆየበት የሩጫ ስፖርት ከመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር አንስቶ፣ በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የትራክ እና የቤት ውስጥ ውድድሮች፣ ከ1 ማይል እስከ 10 ማይል በሚወስዱ ሩጫዎች፣ ከ10 እስከ 25 ኪሎሜትር በሚደርሱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ውድድር ዓይነቶችን በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማግኘት በታሪክ መዝገብ ስሙን ከፍ አድርጎ ያሰፈረ ነው።
 
ከገጠር ቤተሰቦች የተገኘው አትሌቱ ሩጫ ወደ ህይወቱ የመጣው ገና በልጅነቱ ነበር። ታዳጊው ልጅ ያኔ ሩጫን የሚሮጠው በሩጫ ለመለወጥ ሳይሆን የወደፊቱን ህይወቱን እንዲለውጥለት በማለም የተቀላቀለውን የመደበኛ ትምህርት ለመቅሰም በሚያደርገው ትግል ነው።
 
አትሌት ኃይሌ በልጅነቱ ትምህርት ቤት ደርሶ ለመመለስ በቀን 20ኪ.ሜ ለመሮጥ ይገደዳል። ልክ ሰባት ዓመት ሲሞላው “ስለ አንጋፋው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር በሬዲዮ ሰማሁ፤ ስለ እሱ ማሰብ ጀመርኩ። እናም እንደእሱ መሆን ተመኘሁ” ይላል ወደ አትሌቲክስ የገባበበትን አጋጣሚ ሲናገር።
 
“አባቴ የአትሌቲክስን ጥሩነት የተረዳው በስቱትጋርት ዓለም ሻምፒዮን ስንሆን ነው፤ አባቴ የአትሌቲክስ ጥሩነት የተረዳው አንደኛ በመውጣቴ አይደለም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቤታችን ሩጫ በማሸነፍ መኪና ስለገዛሁ እንጂ” በማለት የአትሌቲክስ የስኬት ጅማሮውን ቅቡልነት ይተርካል።
 
ኃይሌን በቅርበት የሚያውቁት የውድድር ተካፋይ ሆኖ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሲቀርብ ፣የሀገርን ክብር እንጂ ገንዘብን እንደማያስብ ይናገራሉ።እርሱም “ከእያንዳንዱ ድል በኋላ ገንዘብ ይከተላል” ይላል።
 
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ፕሬዝዳንት የሆኑት እንግሊዛዊው ሎርድ ሴባስቲያን ኮው በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሰሞን የዓለምን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው ተብሎ ተጠይቆ ነበር።
 
“ሞ ፋራህ የሚደነቅ አትሌት ቢሆንም፤ ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ በረጅም ዓመታት የሩጫ ዘመኑ፣ በብዙ ርቀቶች በመወዳደር እና በተደጋጋሚ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በማስመዝገብ የሚፎካከረው ስለሌለ” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።
 
እ.አ.አ በ1992 በኮሪያ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃትና ጽናት እና ትግስት ሁሌ የሚታወስ ነው። እስከ መጨረሻው ዙር ሲመራ የነበረው ኬንያዊው አትሌት ጆሴፍ አትማቹካ አሸንፍኩ ባለበት ቅጽበት ኃይሌ ያሸናፊነቱን ድል ሲነጥቀው ጀርባውን ባለ በሌለ ኃይሉ የደቃበት የንዴት አገላለጽ እና የኃይሌ ስፖርታዊ ጨዋነት እና ትግስት ለበርካቶች ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነበር። ሮጠው በማይታክቱት እግሮቹ የሀገሩን ሰንደቅዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረገው ሀይሌ ከ1500 ሜትር እስከ ማራቶን ያልነገሰበት የሩጫ ሜዳ የለም።
በ2000 ዓ/ም በተካሄደው የሲድኒ ኦሎምፒክ ኬንያዊውን አትሌት ፖል ቴርጋትን አሸንፎ የወሰደው የወርቅ ሜዳሊያ ከአንበሳ መንጋጋ ስጋን መንጭቆ የማውጣት ያህል የተቆጠረበት ድንቅ ብቃቱን አሁንም ድረስ ዓለም ያስታውሰዋል።
 
ይህን በተመለከተ ኃይሌ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ድሉን ከአርጀንቲናው የማራዶና ጎል ጋር አመሳስሎታል። “በእኔና በፖል ቴርጋት መካከል በነበረው ፍጥጫ በተለይም የመጨረሻዎቹ 100 ሜትሮች አስደናቂ ነበር፡፡ 20 ሜትር እስከሚቀር ድረስ ፖል ቴርጋት ይመራ ነበር፤ፖልን አሸንፌዋለሁ አልልም፡፡ በመጨረሻዎቹ 20 ሜትሮች ነው ፖልን የቀደምኩት። ማራዶና ስላገባት አወዛጋቢ ጎል ተጠይቆ ሲናገር “ ‘የእግዜር እጅ’ አለበት እንዳለው ሁሉ ያንን ውድድር እኔም ያሸነፍኩት ‘በእግዜር እግር’ ነው” ብሏል።
 
በጉልህ ከሚፃፉት ደማቅ ታሪኮቹ በቀዳሚነት ከሚመጡት የስኬቶች መገለጫዎቹ፡-
 
• 2 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት
• 4 የዓለም ሻምፒዮን የወርቅ ሜዳሊያ ባለድል
• አራት የዓለም የቤት ውስጥ የወርቅ ሜዳሊያ ነው
• የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ
ማህበር በድረገፁ ይፋ እንዳደረገው ኃይሌ ገብረስላሴ በሩጫ ዘመኑ በ410 ውድድሮች ያሸነፈ መሆኑን ገልጿል።
• ከአየርላንድ እና ከሊድስ ዩንቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ሽልማት አግኝቷል።
• በረጅም ርቀት ዉድድር የሕይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ከዓለም አቀፍ የማራቶንና የረጅም ርቀት ማኅበር ተበርክቶለታል።
• የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖም አገልግሏል።
• ዛሬ ኃይሌ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በሪል ስቴት፣ በእርሻ፣ በማዕድን፣ በተሽከርካሪ መገጣጠም፣ በታላቁ ሩጫ፣ በኪነጥበብ ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሰ ለሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ እድል በመፍጠር እየተጓዘ ነው ።
• በሚዲያዎችና በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኃይሌ ኢንቨስት አድርጓል።
• ኃይሌና ዓለም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ ማራቶን ሞተርስ፣ ሃዮንዳይ መኪና መገጣጠሚያና በተለያዩ ስያሜዎች በሚጠቀሱ ኩባንያዎቹ ወደ አራት ሺሕ የተጠጉ ሠራተኞችንም ይዟል፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥም የሠራተኞቹን ቁጥር አሥር ሺህ ለማድረስ እቅድ ይዟል።
 የአሸናፊነት መገለጫ የሆነው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከእርሱ በኋላ ለወጡት እነ ቀነኒሳ በቀለና ሌሎችም በጋራ ‘የአረንጓዴውን ጎርፍ’ ታሪክ በመፃፍ አርዓያ ሆኗል። ለሀገሩ ክብርና ኩራት ሲል ህመሙን ታግሶና ችሎ በታላላቅ ውድድሮች ላይ በመሳተፍና ሌሎችን በማበረታታት ለአሸናፊነት አብቅቷል፤ ሀገሩንም አኩርቷል
“ሯጭ ሩጫ የሚያቆመው በሕይወት መኖር ሲያቆም ነው” የሚለው ኃይሌ፣ ከውድድር ቢርቅም በየዕለቱ እንደሚሮጥ ይናገራል።
የኃይሌ ስም ከራስ መጠሪያነት አልፎ የሀገር ምልክት ሆኗል፤ ብዙዎች ከአትሌቲክስ የኃይሌን ያክል ያተረፈ የለም ይላሉ።አትሌቲክስም ከኃይሌ ብዙ አትርፏል።ከሁለቱም በላይ ያተረፈችው ግን ኢትዮጵያ ናት በሚል ሀሳባቸውን የሚያጠናክሩት ብዙ ናቸው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top