ከህዝቡ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ለሁለተኛ ቀን እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው በቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም የምክር ቤት አባላት ጥያቄ አንስተዋል።
በዚህም ሊሰሩ የታቀዱና ተጀምረው የቆሙ የመስኖ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ እና ከኃይል መቆራረጥ በተጨማሪም ቀበሌዎች የመብራት ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢደረግ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
የአማራ ክልል ውሃና ኢንርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ከዚህ በፊት ተገንብተው የተጠናቀቁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በርካታ ቢሆኑም በኃይል አቅርቦት ችግር ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት አልሰጡም።
የህብረተሰቡን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በክልሉ እና በፌዴራል መንግስት በጀት 519 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በጀት ከዚህ በፊት የተጀመሩ 221 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸው 186 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቀሪዎቹም በ2018 እና በ2019 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በህዝቡ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ ሰፊ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንዳሉ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ባለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የመብራት ኃይል ሽፋን ካላቸው ክልሎች አንዱ በመሆኑ አስፈላጊ የመብራት መሰረተ ልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የአካባቢው መስተዳድሮች ሊሰሩ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።