ለመቄዶንያ የተሰበሰበው ብር ከ200 ሚሊዮን በላይ ደረሰ

1 Day Ago 118
ለመቄዶንያ የተሰበሰበው ብር ከ200 ሚሊዮን በላይ ደረሰ
ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ የገቢ ማሰባሰቢ እየተካሄደ በሚገኘው መርሐ ግብር ላይ እስከ ትላንት ሌሊት 12 ሰዓት ድረስ 217 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።
 
መርሐ ግብሩ በትላንትናው ዕለት ለአራተኛ ቀን በቀጥታ ስርጭት ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና የሚዲያ ባለሞያዎች በመድረኩ በመገኘት ለጋሾችን ሲያበረታቱ ውለዋል።
 
"ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው" በሚል መርህ ቃል እየተካሄደ ባለው መርሐ ግብር ሁሉም ወገኖች የሚችሉትን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
 
መቄዶንያ በአዲስ አበባ ዋናው ማዕከል የሚገነባውን ባለ 15 ወለል የአረጋውያን መኖሪያና ዘመናዊ ሆስፒታል ለመጨረስ ፣ተረጂዎችን ከጎዳና አንስቶ በሙሉ አቅም ለመርዳት እንዲሁም በ44 ከተሞች ማዕከላት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
 
ለዚህም የ5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ በይፋ መርሐ ግብሩ ተጀምሯል።
 
በዚህ የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ከጣት ቀለበታቸው እስከ መኖሪያ ቤታቸው በስጦታ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን፣ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል።
 
የታቀደው የ5 ቢሊዮን ብር ጣሪያ እስከሚደርስ ድረስ የገቢ መሳባሰቢያ መርሐ ግብሩ ዛሬም ከደቂቃዎች በኋላ በቀጥታ መተላለፉን የሚቀጥል ሲሆን፣ በጎ ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top