“የጥቁሮች ታሪክ ወር” የጥቁር ሕዝቦችን ውጣ ውረድን፣ ስኬቶችን፣ ታሪክን እና አስተዋፅኦዎችን ለማሰብ የተጀመረ ዓመታዊ የመታሰቢያ ወር ነው።
ይህም በየካቲት ወር በአሜሪካ እና በካናዳ እንዲሁም በጥቅምት ወር በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአየርላንድ እና በሌሎች በርካታ ሀገሮች ይታሰባል።
የዚህ “የጥቁሮች ታሪክ ወር” መታሰቢያ ሀሳብን ያመጡት በአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ ተመራማሪነታቸው "የጥቁሮች ታሪክ አባት" የሚል ስም ያገኙት ዶክተር ካርተር ውድሰን ናቸው።
ውድሰን እ.አ.አ በ1926 የካቲት ወርን "የኔግሮ ታሪክ ወር" ብለው የሰየሙት በጥቁሮች የመብት ትግል ውስጥ በጎ አስተዋፅኦ ያደረጉት 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከን እና የአሜሪካ ማኅበራዊ ተሃድሶ አራማጅ ፍሬድሪክ ዳግላስ ልደት በየካቲት ወር ሁለተኛው ሳምንት መሆኑን ምክንያት በማድረግ ነበር።
እንቅስቃሴው በሂደት በበርካቶች ዘንድ እውቅናን እያገኘ መጥቶ እ.አ.አ በ1976 በ38ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጄራልድ ፎርድ አማካኝነት በአሜሪካ ውስጥ በየዓመቱ እንዲታሰብ በይፋ ታወጀ።
በመቀጠልም ካናዳ በ1995፣ ዩናይትድ ኪንግደም በ1987፣ እንዲሁም አየርላንድ በ2014 “የጥቁሮች ታሪክ ወር” ለአፍሪካ ዳያስፖራ ላደረገው በጎ አስተዋፅኦ እውቅና በመስጠት በየሀገሮቻቸው እንዲታሰብ አድርገዋል።
“የጥቁሮች ታሪክ ወር” ዓለማ ጥቁሮች ለዓለም ያበረከቱትን አስተዋፅኦ፣ የጥቁሮችን የመብት ትግል ምንነት ለሌሎች ለማስተማር እና እንደነ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ሮዛ ፓርክ፣ ማልኮም ኤክስ እና ሃርየት ተምብማን ያሉ የጥቁሮች መብት ተከራካሪዎችን ማሰብ እንደሆነ ይነገራል።
ዋናው ዓለማው ግን በየሀገራቱ ያለውን ሥርዓታዊ ዘረኝነትን ጎላ አድርጎ ለማሳየት እና ሁሉም የሰው ዘር ፍትሕን እና እኩልነትን እንዲጎናጸፍ ማስቻል ነው።
ወሩ ሲከበር የጥቁሮችን ፍትሕ፣ የጥቁሮችን ጤና እና ደኅንነት፣ የጥቁሮችን ሰብዓዊ መብት እና አጠቃላይ የጥቁሮችን የእኩልነት ጥያቄ የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ጭብጦችን በመያዝ ሲሆን፣ ለጥቁሮች መብት መከበር አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች ይታወሱበትል።
እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ሮዛ ፓርክ እና ማልኮም ኤክስ ያሉ የሰብአዊ መብት መሪዎች፣ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን ካርቨር፣ ማዳም ሲ ጄ ወከር እና ጋሬት ሞርጋን ያሉ ጥቁር የፈጠራ ሰዎች፣ እንደ ማያ አንጄሉ፣ ጀምስ ባልድዊን፣ ቶኒ ማሪሰን ያሉ የጥቁር ባህል አቀንቃኞች ጥበበኞች እንዲሁም እንደነ ባራክ ኦባማ፣ ካማላ ሃሪስ እና ኔልሰን ማንዴላ ያሉ ጥቁር የፖለቲካ መሪዎች በዚህ ወር ይታሰባሉ።
ወሩ ከላይ የተዘረዘሩ ዓላማዎችን በማጉላት በትምህርት ተቋማት፣ በሚዲያ እና ፊልም ማዕከላት እና በማኅበረሰብ ውስጥ ተለያዩ ሁነቶችን በመፍጠር እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎትን በመስጠት ይከበራል።
ጥቁሮች የጠየቁትን መብት አግኝተዋል?
በአሜሪካ እና በሌሎች የሀገራት ሕገ መንግሥታት እና ሌሎች ሕጎች በሀገራቸው የሚኖሩ ዜጎች እኩልነት የማይታበል መሆኑን በግልጽ ቢያስቀምጡም ሥርዓት ወለድ ጭቆናው ግን አሁንም እንዳልተፈታ ይገለጻል።
በርካቶች አሁንም ሥርዓት እና ማኅበረሰብ ወለድ የጥቁሮች ጭቆና እንዳልቀረ ይናገራሉ። ለዚህም በአሜሪካ ጥቁሮች እና በሌሎች ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት እንደማሳያ ያቀርባሉ።
‘ብላክ ዎል ስትሪት፣ ሴኔካ ቪሌጅ፣ ሮዝውድ፣ ኦስካርቪል፣ በላክዶም፣ ቫንፖርት እና ፕሪንስቪል’ ያሉ የጥቁሮች መኖሪያ አካባቢዎች በአንድ ወቅት የበለጸጉ የነበሩ ግን ከጊዜ በኋላ እንዲጠፉ የተደረጉ ናቸው።
እንደ ‘አፍሪካ ታዎን፣ ዘ ብላክ ቤልት፣ ሳውዝ ሳይድ ቺካጎ፣ ሃርለም፣ ኦቨርታዎን፣ ፎርዝ ዋርድ፣ ኢስት ሴንት ሉዊስ’ ያሉት የጥቁሮች መኖሪያ አካባቢዎች ደግሞ ሆን ብለው የተረሱ ናቸው። እነዚህ አካባቢዎች እንደ አደገኛ ስፍራ ስለሚታዩ ማንም ወደዚያ አካባቢ እንዲሄድ አይፈቀድም። ጥቁር ኗሪዎች በተለይም ወጣቶች በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የተጠቁ፣ ብዙም ትምህርት የማይገፉ እና እስከነጭራሹም ያልተማሩ ናቸው። እነዚህ መንደሮች ባህላቸውን እና ማንነታቸውን ጠብቀው እንዲያድጉ እና ከሌላው ማኅበረሰብ እኩል ትኩረት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ማግለል ይመረጣል።
ይህ ማኅበረሰብ እና ሥርዓት ወለድ ማግለል ግን በዘላቂነት የሚፈታው ብሶትን በማስተጋባት እንዳልሆነ የጥቁሮች በመብት ተከራካሪዎች ይናገራሉ። ለዚህም በአንድ ወቅት ከጥቁሮች እኩል ስለ መብታቸው ሲጮኹ የነበሩት አይሁዶች ከጥቁሮች የተሻለ መብት ከማግኘት አልፈውም በአሜሪካ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ቦታ መያዛቸውን፣ በአንጻሩ ደግሞ ጥቁሮች ዛሬም በዘር መድልኦ እየተገፉ መሆናቸው እንደማሳያ ይነሣል።
ከጥቁሮች እኩል በማንነታቸው ሲገፉ የኖሩት አይሁዶች አሁን ያላቸውን ተፅዕኖ ያገኙት የትግል ስልታቸውን ከመቀየራቸውም በተጨማሪ የቀለም ልዩነታቸውም እንደጠቀማቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። 2.4 በመቶ ብቻ የሚሆኑት አይሁዶች ‘ተጨቆንን’ የሚለውን የትግል ስልት ቀይረው አንገታቸውን ደፍተው በመሥራት በአሜሪካ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መግባታቸው ለዛሬው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሲያበቃቸው፣ ከአሜሪካ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ከ13 በመቶ በላይ የሚይዙት ጥቁሮቹ በአንጻሩ አሁንም ብሶታቸውን ብቻ ማስተጋባት መቀጠላቸው እውነተኛ መብት እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
ጠንካራ የጥቁሮች መብት ተከራካሪ የሆነው ማልኮም ኤክስ በበኩሉ የጥቁሮች መብት ተሟልቶ ያልተከበረው በራሳቸው በጥቁሮች ክፍፍል ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ነበር። እ.አ.አ በ1963 ባደረገው “Message to the Grassroots” በተባለው ዝነኛ ንግግሩ ባሪያዎችን "የቤት" እና "የሜዳ" ("House Negro" and the "Field Negro") በማለት በሁለት ከፍሏል። እንደ እሱ ንግግር የቤት ባሪያዎች ብርድ እና ፀሐይ የማያገኛቸው፣ ከጌቶቻቸው የተረፈ ምግብ የሚመገቡ፣ የጌቶቻቸውን ሰፋፊ ልብሶች የሚለብሱ በዚህም ምክንያት “ጌቶቻቸው ሲታመሙ የሚታመሙ” ናቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥቁሮች በጌቶቻቸው ችሮታ ከሚያገኟቸው ነገሮች ባሻገር ያለውን ሰው የመሆን መብቶች ስለማይረዱት ጥቁሮች ሙሉ መብት ለማግኘት የሚያደርጉትን ትግል ያደናቅፋሉ። ወደ ፖለቲካው መድረክ የሚመጡትም በነጮቹ ታማኝነትን ያገኙት እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥቁሮች በመሆናቸው ወገኖቻቸው ላይ የሚደርሰውን ስውር ጫና ለመቃወም አቅም አይኖራቸውም።
ማልኮም ኤክስ የውጭ ባሮች ያላቸው ደግሞ በተለያዩ ከባድ ሥራዎች ላይ ተጠምደው የኖሩትን ነው። እነዚህ በመከራ ውስጥ ያለፉ ጥቁሮች ዛሬም እውነተኛ መብት አላገኙም። በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ጥቁሮች የመምረጥ፣ የመመረጥ እንዲሁም ከሌሎች እኩል የመኖር መብት አላቸው ቢባልም በሥርዓቱ ውስጥ እኩል እንዳይሳተፉ ግን ስውር ሥርዓታዊ እና ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖ ይደረግባቸዋል።
ለዚህም ነው እንደ ማልኮም ኤክስ ያሉት የጥቁሮች መብት ታጋዮች በወረቀት ላይ በተጻፈ ሕግ ብቻ የጥቁሮች መብት ተከብሯል ማለት እንደማይቻል የሚያወሱት። “የጥቁሮች ታሪክ ወር” መታሰቢያ ብቻ ሆኖ ማለፍ ሳይሆን ሰዎች እውነተኛ መብታቸውን የሚጎናጸፉበት ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ ችግሩ ከመሠረቱ እንዲፈታ የሚሹ ወገኖች።
በለሚ ታደሰ