ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ልዩ እና ጉልህ ስፍራ አላት። ቅኝ ሊገዟት የሞከሩት እንኳን በጻፏቸው የታሪክ ድርሳናት ይህንን ታላቅነቷን በሰፊው ተርከዋል።
ኢትዮጵያ ብዙዎችን የዓለም ሀገራት ባስደመመ ሁኔታ በቅኝ አለመገዛቷ ለአፈሪካውያን የነፃነት እንቅስቃሴዎች ትልቅ ተነሣሽነት ነበረው።
ይህ የኢትዮጵያ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ሚና እና ጠንካራ የቅኝ ገዢዎች የተቃውሞ ታሪክ በሀገራችን ማንነት ላይ ጠለቅ ያለ፣ የራሱን ብሔራዊ እና አዎንታዊ ትርክት ከመፍጠሩም በሻገር የአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ ትግል ላይም እጅግ ግዙፍ ተፅዕኖ አሳድሯል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የምትታወቅበት አንደኛው የጣሊያን እና የኢትዮጵያ ጦርነት (1888) ዓ.ም ውስጥ መከሰት ነበር። በወቅቱ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀራመቱ ነበር፤ በዚሁ መሠረት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግዛቷ ውስጥ ለማካተት በማሰቧ በ1888 የዓድዋ ጦርነት መከሰቱ የሚታወስ ነው።
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ጦር የጣሊያንን ጦር በቆራጥነት በማሸነፍ አስደናቂ እና ታሪካዊ ድል አስመዝግቧል። ይህ ድል የኢትዮጵያን ነፃነት በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቅኝ ግዛትን በመቃወም የተቃውሞ ምልክት እና ጉልበት ሆኗል።
የኢትዮጵያ የዓድዋ ድል፣ በተክኖሎጂ የላቀውን የአውሮፓ ኃይሎች፣ የአፍሪካ ኃይሎች በሚገባ በመደራጀት እና በወኔ በተሳካ ሁኔታ አውሮፓን መዋጋት እና ማሸነፍ እንደሚችል ያሳየ ነው።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ያስጠበቀች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ለሌሎች በቅኝ ግዛት ስር ላሉ ሀገራት የተስፋ ብርሃን እንድትሆን አድርጓታል። በቅኝ ያልተገዛው ታሪኳ ለሰፊው አፍሪካዊ የነፃነት ትግል ኩራት እና መነሣሣትን የፈጠረ ነበር።
በፓን አፍሪካኒዝም ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና፣ በአፍሪካ መንግሥታት መካከል አንድነትን የሚያበረታታ የፖለቲካ እና የባህል ንቅናቄ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው።
በ1923 ዓ.ም ዙፋኑን የተረከቡት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበሩ። በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ሲመሠረት የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ራዕይ መሠረት ነበረው።
በሁለተኛው የጣሊያን እና ኢትዮጵያ ጦርነትም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ወቅት የአፄ ኃይለ ሥላሴ መሪነት ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እና ለነፃነት ትግሉ የነበራትን ሚና ማጠናከርዋን አሳይቶ ነበር።
ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) እና የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
እንዲሁም ከቅኝ አገዛዝ ጋር ለሚዋጉ ሀገራት የሞራል እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ለአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴዎች መድረክ ሆኖ አገልግሏል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ መውጣት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ ፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ረገድ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።
ሀገሪቱ በኬንያ፣ በአልጄሪያ እና በደቡብ አፍሪካ ያሉትን ጨምሮ ለብዙ የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄዎች፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች። የኢትዮጵያ ጥረት የበርካታ አፍሪካ ሀገራትን ነፃነት እንዲጎናፀፍ አግዟል።
ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ላይ የነበራት ተቃውሞ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመፍጠር ረገድ የተጫወተችው ሚና ለዘመናዊው አፍሪካዊ ማንነት መቀረጽ መሠረት ሆኗል።
ሀገሪቱ በአፍሪካ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ልዩ ቦታን እንድታገኝ ያደረገችው በታሪካዊ ሚናዋ ብቻ ሳይሆን በባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ፋይዳዋም ጭምር ነው።
የፓን አፍሪካኒዝም መፍለቂያ እንደመሆኗ፣ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ያደረገችው አስተዋፅኦ በአህጉሪቱ የጋራ ንቃተ ኅሊና ላይ የማይጠፋ አሻራ ጥሏል።
ሀገሪቱ በቅኝ ያልተገዙ ቅርሶቿ ላይ ያላት ኩራት የአፍሪካ መንግሥታትን አንድነት እንዲሁም ለራስ ጉዳይ በራስ የመወሰን መብትን የሚደግፉ እንቅስቃሴዎችን ማነሣሣቱን ቀጥሏል።
በአጠቃላይ ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦርነት ታሪካዊ ድል ድረስ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢ ኃይሎች ላይ ያደረገችው ተቃውሞ እና ትግል፣ ትሩፋቱ ለአፍሪካ አገሮች የተስፋ ብርሃን ሆኗቸዋል።
ለመረጃው በተክለ ጻድቅ መኩሪያ የተጻፈው የኢትዮጽያ ታሪክ እና በኤመሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተጻፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 እንዲሁም የሪቻርድ ፖንክረስት The Ethiopians መጽሐፍትን ዋቢ አድርገን ተጠቅመናል።
በሔለን ተስፋዬ