ባለፉት 5 ወራት ብቻ 15 ቢሊዮን ብር ከኮንትሮባንድ ማዳን መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የአትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ባዘጋጀው 3ኛው አገር-አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ስብራት መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ይህን ለመቆጣጠር ባለፉት 5 ወራት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
በዚህም በገቢ ንግድ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ፤ በወጪ ንግድ እንዲሁ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ከኮንትሮባንድ ማዳን መቻሉን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው፤ የመድረኩ መዘጋጀት ህገ-ወጥ ንግድ በመደበኛው የንግድ ስርዓት ብሎም በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ተጽዕኖን ከተለያዩ ሴክተሮች አንጻር ለመዳሰስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማሳየት እና ችግሩን ለመቆጣጠር ውይይት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በህይወት አበበ