የኮሪደር ልማት ስራው የሐረር ከተማን ለነዋሪዎቿ እና ጎብኚዎች ምቹ እንድትሆን የሚያስችል ነው ፡-አቶ ሙክታር ሳሊህ

1 Day Ago 69
የኮሪደር ልማት ስራው የሐረር ከተማን ለነዋሪዎቿ እና ጎብኚዎች ምቹ እንድትሆን የሚያስችል ነው ፡-አቶ ሙክታር ሳሊህ
የኮሪደር ልማት ስራው የሐረር ከተማን ለነዋሪዎቿ እና ጎብኚዎች ምቹ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዕረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
 
በሐረሪ ክልል በሁለተኛ ዙር የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ማስፈፀሚያ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
 
የኮሪደር ልማቱ ፕሮጀክቶችን አቅዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የይቻላል መንፈስ እውን የሆነበት ብሎም የስራ ባህል እንዲጎለብት ያስቻለ መሆኑን አቶ ሙክታር በዚህ ወቅት ገልፀዋል።
 
በመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ከፍተኛ አመራሩ በጥብቅ የሥራ ዲስፕሊን በመመራት ባደረገው የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል በተሞክሮነት ሊጠቀስ የሚችል አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
 
በተለይ የኮሪደር ልማት ስራው ከተማውን ለዜጎች ምቹ መኖሪያ እና የስራ አካባቢ እንዲፈጠር ያስቻለ መሆኑን በመጠቆም ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
 
የሐረር ከተማ ቱሪዝም መዳረሻ እንደመሆኗ መጠን የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ምቹ እና በቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻነቷን የሚያጎለብት መሆኑንም አንስተዋል።
 
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እና የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አክለዋል።
 
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የተገኙ ተመክሮዎችን በመቀመር በሁለተኛው ዙር በከተማና ገጠር የሚከናወኑ ማስፋፊያዎችን በአጭር ጊዜ በጥራት እና ፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
 
ለስራው ውጤታማነት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ ቡድን በሁሉም ወረዳዎች የድጋፍና ክትትል ስራ እንዲያከናውን መመደቡንም ገልጸዋል።
 
በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top