ቀይ ባሕር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ ያለው የባሕር ላይ ውንብድና ኢትዮጵያን ያሳስባታል፡- አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

3 Hrs Ago 30
ቀይ ባሕር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ ያለው የባሕር ላይ ውንብድና ኢትዮጵያን ያሳስባታል፡- አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፥ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በአካባቢው ባሕር ላይ ያለው የሰላም ሁኔታ ተፅዕኖ ይፈጥርባታል።
 
አምባሳደር ታዬ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ ግጭት፣ የባሕር ላይ ውንብድና እና ሌሎች ፈተናዎች መለያው እየሆነ መጥቷል።
 
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በአካባቢው ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን በብቃት ስትከላከል ኖራለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆን አካባቢው ሰላም በሚሆንበት ሂደት ላይ የራሷን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች ብለዋል።
 
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉንም የአካባቢውን ሀገራት ያሳተፈ የትብብር እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ እንደምታምን ተናግረዋል።
 
በሌላ በኩል አሸባሪነት የምሥራቅ አፍሪካ አሳሳቢ የሰላም እንቅፋት እየሆነ ይገኛል ያሉት አምባሳደር ታዬ፣ እንደ አልሸባብ ያሉ ፅንፈኞች በአካባቢው ሰላማዊ ሰዎች ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት እጅግ እየጨመረ እንደመጣ ገልጸዋል።
 
አሁን የሶማሊያ መንግሥት እያሳየው ያለው የኢትዮጵያ፣ የቡሩንዲ፣ የኬንያ እና የኡጋንዳ ልጆችን መስዋዕትነት ከንቱ ያደረገ እንቅስቃሴ የሶማሊያን ሕዝብ ለአደጋ እያጋለጠው እንደሚገኝም ነው ሚኒስትሩ ያወሱት።
 
ይህ እንቅስቃሴ ተመድ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋግጥ የሚያደርገውን ድጋፍም በከንቱ የሚያስቀር ስለሆነ፤ የሶማሊያ መንግሥት ወደ ትክክለኛ መስመር ተመልሶ ለአካባቢው ሰላም የራሱን ድርሻ ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር ስምምነት መነሻው አሁን በአካባቢው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ስምምነቶችን ሲያደርጉ ዝምታን የመረጠው የሶማሊያ መንግሥት አሁን እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ ጥያቄ የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ ዓላማ የቀጣናው ትብብር እና አብሮ ማደግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሶማሊያ መንግሥት ግን ይህን የኢትዮጵያ አቋም በጭራሽ ከግምት ማስገባት አልፈለገም ብለዋል።
 
አሁንም ኢትየጵያ የሶማሊያ መንግሥት የሚያደርገውን ጸብ አጫሪ ድርጊት ወደ ጎን ትታ ለጋራ ሰላምና ዕድገት እየሠራች እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ወደ ትብብሩ ተመልሶ ቀጣናውን እያመሰው ያለውን ሽብር በጋራ ለመከላከል እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
 
ከቀጣናው ውጭ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያን የሰላም ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ጸብ ጫሪ ድርጊት ውስጥ እየገቡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን አሁንም በእነዚህ አካላት ትንኮሳ አሸባሪነትን ከመዋጋት ለአፍታም አትዘናጋም ብለዋል።
 
እነዚህ ከቀጣናው ውጭ እየመጡ አካባቢውን የሚያውኩት አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የጠየቁት አምባሳደር ታዬ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ኃላፊነት በጎደለው የነዚህ ወገኖች እንቅስቃሴ የሚፈጠረውን ቀውስ ከግምት ውስጥ አስገብተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top