የመስከረም ስጦታው የሙዚቃ ንጉሥ፦ መስከረም ለኢትዮጵያ የለገሰችው እንዲህ እንደሚንቆለጳጵሳት አውቃ ይሆን?

2 Days Ago 254
የመስከረም ስጦታው የሙዚቃ ንጉሥ፦ መስከረም ለኢትዮጵያ የለገሰችው እንዲህ እንደሚንቆለጳጵሳት አውቃ ይሆን?

ለግማሽ ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ግንባር ቀደም ሆኖ ካለፉት ኮከቦች መካከል አንዱ ነበር፤ ለዚህም ነው "የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ" የሚል መጠሪያ የተሰጠው፡፡

"በፀሐይ ብርሃን ደምቃ፣ ክረምትና በጋ፤

የትውልድ አገር ያላት፣ የአስራ ሦስት ወር ጸጋ፤…" በሚለው እና ከመስከረም ጀምሮ እስከ ቡሄ በሚዘልቀው ዜማው የኢትዮጵያውያንን ውብ የዓውደ ዓመት አከባበር ባህል በአእምሮአችን የሚስልልን ባለዜማን መስከረም ለኢትዮጵያ የለገሰችው እንዲህ እንደሚንቆለጳጵሳት አውቃ ይሆን ያስብላል! ጥላሁን፦

"አቤት በአዲሱ ዓመት - ዘመኑ ሲለወጥ፣

ያበቦቹ ሽታ - መዓዛው ሲመስጥ፤

ኮበሌውም ሲጨፍር - ሲል መስከረም ጠባዬ፤

ኮረዳዋም ባቅሟ - ስትዞር በራሷ ቀዬ፤…" እያለ ነው ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ለአዲስ ህይወት እና አዲስ ተስፋ ጅማሮ እንደ ንጋት የሚቀበሏትን መስከረም ያወሳት፡፡

አንድ ዓመት እስኪሞላው ድረስ መጠሪያ ስሙ ሴት አያቱ ያወጡለት "ደገፉ" የሚለው እንደነበር በህይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡ አያቶቹ ሙስሊሞች እንደነበሩ የሚነገርለት ደገፉ በተወለደ በአንድ ዓመቱ መስከረም ወር ወሊሶ ከተማ በምትገኘው ቤተሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ቤተክርስቲያን ክርስትና ተነሳ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የክርስትና አባቱ ቀኝአዝማች መኮንን መሸሻ የከበረበትን እና የብዙዎች መጠሪያ የሆነውን "ጥላሁን" የሚለውን ስም ያወጡለት፡፡

ዘካሪያ መሐመድ በጻፈው የህይወት ታሪኩ ላይ እንደተጠቀሰው ጥላሁን "መሳቁን ይስቃል" እና "ሀርካ ፉኔ" የሚሉ ዘፈኖችን ሲዘፍን እንባው የሚፈስሰው በሰው እጅ የተገደሉትን እናቱን እያስታወሰ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ስለሚገባ ነበር። ይህ ስሜቱም በሠርግ እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ተጋብዞ የሚያቀርባቸው ዘፈኖች በለቅሶ እና እንባ የታጀቡ እንዲሆኑ አድርጎት ነበር። በዚህም ምክንያት ታዳሚውን ለማዝናናት ሄዶ በማዝናናት ፈንታ እያስቆዘመ እንደሆነ ጠቅሰው ለሚገስጹት ወዳጆቹ ሲመልስ፣ “ወድጄ እኮ አይደለም፤ እኔ እዚህ ቆሜ እዘፍናለሁ፤ ይኼኔ የእናቴ ገዳይ በነጻነት ይዝናናል፤ ፍርድ ሳላገኝ   እንዴት ለቅሶዬን ላቆም እችላለሁ” ይል ነበር።

ጥላሁን ስለ እናቱ ገዳይ እንደዚህ ሲብሰለሰል ቢኖርም ከብዙ ማፈላለግ በኋላ የእናቱ ገዳይ ወሊሶ ከተማ ውስጥ እንደሚኖር ሲያውቅ ግን ለበቀል ከመዘጋጀት ይልቅ "ይቅር ብየዋለሁ" በማለት ነበር ታላቅ ስብእናውን ያረጋገጠው።

ሙዚቃ ለጥላሁን ገሠሠ ሥራው ሳትሆን ህይወት እና ተስፋው ነች፡፡ መከፋቱን የሚረሳባት፣ ትዝታውን የሚኖርባት፣ ስሜቱን የሚገልጽባትም ነች፡፡ ለዚህም ነበር ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ አንድ ወቅት ባደረገችለት ቃለ መጠይቅ ከሙዚቃ ጋር ያለውን የህይወት ቁርኝት ሲያብራራ፣” ከሙዚቃ ለሰከንድ መለየት አልፈልግም፤ የሙዚቃ መሣሪያ ጋጋታው እንኳ ቢቀር ቤቴ ውስጥ አንጎራጉራለሁ፤ እኔ የእናቴን ሕይወት የለወጥሁት በሙዚቃ ነው” ያለው።  

የጥላሁን ህይወት ምስጢር ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያው ሚያዝያ 10 ቀን 1985 ዓ.ም የትንሳኤ ዕለት የደረሰበት አደጋ ነው፡፡ በዕለቱ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ እያለ ሆዱን፣ ጉሮሮውን እና እጁን ተወግቶ ዘውዲቱ ሆስፒታል ገባ። ለተሻለ ህክምናም ወደ እንግሊዝ ሀገር ተወስዶ ህይወቱ ተርፎ ተመለሰ። በወቅቱም ብዙዎች ስለ አደጋው ምስጢር ለማወቅ ብዙ መላ ምት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ጥላሁን ግን ሙሉ በሙሉ ከዳነ በኋላ አደጋውን ማን እንዳደረሰበት ሲጠየቅ “ሆድ ይፍጀው” ብሎ አለፈው። ምስጢሩንም ይዞት ወደማይቀረው ዓለም ስለሄደ እስከ ዛሬ እንቆቅልሹ ሳይፈታ እነሆ አለ።

ጥላሁን ተፈጥሮ ያለስስት በለገሰችው ድምፁ ያላነሳው ሀሳብ ያላንጎራጎረው ጉዳይ የለም፡፡ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች እና ከፀሐይ በታች ያሉት ጉዳዮች ሁሉ በጥላሁን ዜማዎች ተዳስሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ የጥላሁንን ያክል ደማቅ አሻራን ያሳረፈ ትውልድን ተሻጋሪ ድንቅ እና ተደማጭ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተ ድምጻዊ ያለ አይመስልም።

"አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ፣

በዘፈን አንደኛ ጥላሁን ገሠሠ" የተባለለት ድምፀ መረዋው ጥላሁን ገሠሠ! ልክ የዛሬ 83 ዓመት መስከረም 17 ቀን በወሊሶ አውራጃ፣ ጎሮ ወረዳ፣ ሶየማ ቀበሌ፣ ወ/ሮ ጌጤነሽ ኢተአ ወንድ ልጅ ተገላገሉ። ጥላሁን ከተወለደ በኋላ ወ/ሮ ጌጤነሽ ከባለቤታቸው አቶ ገሠሠ ወልደኪዳን ጋር የእናታቸው ርስት ወደሚገኝበት አመያ ሄደው መኖር ጀመሩ። ለአምስት ዓመታት ከኖሩ በኋላ ግን በ1938 ዓ.ም ወ/ሮ ጌጤነሽ ወደ የት እንደሄዱ ሳይታወቅ ጠፉ።

አባቱ አቶ ገሠሠ በበኩላቸው ሕጻኑን ጥላሁንን ለአያቱ ትተው ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ። አያቱ ጋር የቀረው ጥላሁን በ1939 ወሊሶ ከተማ በሚገኘው ራስ ጎበና ዳጨው ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ። ጥላሁን ትምህርቱን በወሊሶ ሲጀምር አያቱ ወ/ሮ ነገዬም ከጥላሁን ጋር በወሊሶ ቤት ተከራይተው መኖር ጀመሩ። የወላጆቹ ጥለውት መሄድ ተፅዕኖ ያሳደረበት የሚመስለው ጥላሁን ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ ወደ እንጉርጉሮ ያደላ ነበር።

ትምህርት ቤቱ ውስጥ የተለያዩ መዝሙሮችን በማዳመጥ አጥንቶ ይዘምር ነበር። ይህን ያዩት የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሱዳናዊው ሚስተር ሸዳድ በአድናቆት አበረታቱት። ወንድማቸው ማህሙድ ሳንሁሪም ደግሞ ቤቱ እየወሰደ በሸክላ የተቀረፁ ዘፈኖችን ያስደምጠው ነበር። ጥላሁንም የሰማውን በቃሉ ይዞ ማንጎራጎር የዘወትር ተግባሩ።

ጥላሁን የአምስት ዓመት ሕጻን ሳለ ድንገት የጠፉት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ጌጤነሽ አዲስ አበባ እንዳሉ ተሰማ። ከእናቱ ጋር እንዲገናኝ ተብሎ በ1943 ወደ አዲስ አበባ መጣ። እናቱን ካገኘ በኋላ ትምህርቱን እንዲቀጥል ወደ ወሊሶ እንዲመለስ ቢደረግም፣ ልቡ ወደ አዲስ አበባ የሸፈተበት ጥላሁን ወደ አዲስ አበባ በእግር ጉዞ ለማድረግ ሞክሮ ቱሉ ቦሎ ላይ ተይዞ እንደተመለሰ ራሱ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓውደ ሰብ በሰጠው ቃለመጠይቅ ተናግሯል፡፡ የመጀመሪያው ሙከራ ያልተሳካለት ጥላሁን በሌላው ቀን በጭነት መኪና ላይ ተደብቆ ተጓዘ፡፡ በዚህም መሰረት በ1944 ጠቅልሎ ወደ አዲስ አበባ ገባ።

በ1947 ሀገር ፍቅር ማኅበር ተቀጠረ። በሀገር ፍቅር ቆይታውም ከኢትዮጵያ ሙዚቃ መሠረታዊ ቅኝቶች ጋር ለመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል። ‘ጥላ ከለላዬ’፣ ‘ጽጌረዳ ነሽ’፣ ‘ደጉ ንጉሥ’ እና ‘ፍቅሬ ሰውነቴ’ የተሰኙ ዘፈኖችን በመዝፈን ከሕዝብ ጋር የተዋወቀው በሀገር ፍቅር ነበር። በሀገር ፍቅር ማኅበር እያለ የኢዩኤል ዮሐንስ ድርሰት በሆነው "መንገድ ሰማይ" በተሰኘው ተውኔት "ቅድስት ነፍስን" ወክሎ እንደተወነ ይነገራል፡፡

የጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃ ክህሎት ደምቆ መውጣት የቻለው ግን በ1948 በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራን ከተቀላቀለ በኋላ ነው። ወደ አስር ዓመታት በዘለቀው የክብር ዘበኛ ቆይታው ኦርኬስትራው አጃቢነት ድንቅ ዘፈኖችን ተጫውቷል። በወታደራዊው ደርግ ዘመን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ባንድ ተብሎ ከተሰየመ በኋላም፣ ጥላሁን የባንዱ ኮከብ ድምጻዊ ሆኖ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ ቆይቷል።

ጥላሁን ከክብር ዘበኛ ባንድ በተጨማሪ በተለያዩ ኦርኬስትራዎች እና ባንዶች ታጅቦ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለሕዝብ አድርሷል። “ጩኸቴን ብትሰሙ”፣ “እኔ ነኝ ወይ አንቺ”፣ “አይከዳሽም ልቤ” እና “ማስታወሻ”ን የዘፈናቸው በምድር ጦር ኦርኬስትራ አጃቢነት ነበር፡፡ “ሰው ማንን ይመስላል” እና “ስማ” የተሰኙ ሁለት ሙዚቃዎችን ደግሞ ያቀረበው በፖሊስ ኦርኬስትራ አጃቢነት ነበር፡፡ “በይ ደህና ክረሚ” እና “ስንብት” የተሰኙ ሁለት ዘፈኖችን የተጫወታቸው ደግሞ በሬይንቦው ባንድ አጃቢነት ነበር። “የኔ ፍላጎቴ” እና “በደህና እስኪገጥመን” የሚሉትን ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ ያጀበው ኤግዚቢሽን ባንድ ነው፡፡ “ኩሉን ማን ኳለሽ” ፣ “አለኝታዬ”፣ “ላንቺ ብዬ”፣ “ስትሄድ ስከተላት”፣ “ትዝ አለኝ የጥንቱ” እና “የሀገሬ ሽታ”ን በሙላቱ አስታጥቄ ኦል ስታር ባንድ ታጅቦ ተጫውቷል። “ውበትሽ ይደነቃል”፣ “ጽጌረዳ”፣ “አካም ነጉማ”፣ “የቆለኛ ልጅ”፣ “ፍቅሬ ሆይ ያላንቺ” እና ሌሎች ሙዚቃዎች የሚገኙበትን ካሴት ከአይቤክስ ባንድ ጋር ሠርቷቸዋል።

“የ13 ወር ፀጋ” እና “እንቆቅልሽ” የተሰኙትን ካሴቶች ከሮሃ ባንድ ጋር ነው የሠራቸው። ሮሃ ባንድ ከብዙነሽ በቀለ፣ ማህሙድ አሕመድ እና ሒሩት በቀለ ጋር በጋራ ያወጡት ካሴትም አጅቧቸዋል። ”ከሌለህ የለህም” እና የ”ይቺ ናት ጨዋታ” አልበሞችን ደግሞ ከዋሊያስ ባንድ ጋር ነው የሠራቸው።

ጥላሁን ከኦርኬስተራዎች እና ባንዶች በተጨማሪም በምሽት ቤቶች እየተዘዋወረ ተወዳጅ ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ እንደነበር የህይወት ማህደሩ ያሳያል፡፡ አሪዞና፣ አክሱም እና ፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ቤቶች የጥላሁንን የሙዚቃ በረከት ከተቋደሱት የምሽት ክበቦች መካከል ናቸው፡፡

ጥላሁን ወደ ሃምሳ ዓመታት በተጠጋው የሙዚቃ ሕይወቱ የተጫወታቸው ዜማዎች፣ የየዘመኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ማኅደሮች ነበሩ። ሙዚቃዎቹ ፍቅርን ከመስበክ ባሻገር የማኅበረሰብን ችግሮች ነቅሶ በማሳየት የሚያስተምሩም ነበሩ።

ሙዚቃዎቹን ሲሠራቸው ከልቡ ተቀብሏቸው ስለሆነ እንደሚያነሳው ጉዳይ ስሜቱን ይለዋውጣል፡፡ ለዚህ ነው ጥላሁን ሙዚቃን በተግባር ይኖራታል የሚባለው፡፡ የሚዘፍነው ስለፍቅር ሲሆን የፍቅር ስሜት፣ ስለ ሀገር ሲሆን በልዩ ተመስጦ፣ ስለሚያሳዝን ጉዳይ ሲሆን በእንባ ታጅቦ ነው፡፡ ልቡ ምን ያክል ስስ እንደሆነ እና የሕዝቡ ጉስቁልና እንደሚያምመው ያሳየው የወሎን ርሃብ ካየ በኋላ ያዜመው "ዋይ ዋይ ሲሉ" የሚለው ሙዚቃው ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ሙዚቃው፡-

"ዋይ ዋይ ሲሉ፣

የርሀብን ጉንፋን ሲስሉ፣

እያዘንኩኝ በዓይኔ አይቼ፣

ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ፡፡

ወይ እማማ ወይ አባባ፣

ብለው ሲሉ ሆዴ ባባ፣

አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፤

ምንስ ሆኜ ምን ላድርጋቸው፣

ሳያቸው አይኔ አፍጥጦ፣

ተለየኝ ልቤ ደንግጦ፣

ተብረከረከ ጉልበቴ፣

ምን ላድርግ ዋ! ድህነቴ፡፡ …"

ብሎ የውስጡን ሀዘን እና በርሃብ በተጎዱ ሰዎች ምክንያት የተሰማውን ስሜት ይገልጽና፡-

"…በዚህች ድልል ከንቱ ዓለም

መቼም ጠገብኩ የሚል የለም

የተገኘውን እንስጣቸው

ቸርነቱን አንንሳቸው፡፡…" በማለት ለነዚህ ወገኖች መድረስ እንደሚገባ ጥሪ ያቀርባል፡፡ የሕዝብን መከፋት አይቶ ማለፍ እንደማይሆንለት ይህ ሥራው አንዱ ምስክር ነው፡፡

በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ በነበረበት ዘመን የተወሰኑ የተመረጡ ዘፈኖቹ በብሔረ ጽጌ መናፈሻ ተቀርፀው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1964 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሕዝብ ቀርበዋል።

በንጉሡ ዘመን ጥላሁን በሚሠራቸው እንዳንድ ሙዚቃዎች የሳንሱር ሰለባ መሆኑ አልቀረም፡፡ የሳንሱር ሰለባ ከሆነባቸው ሙዚቃዎች መካከልም በ1956 ዓ.ም ለሕዝብ ያቀረበው "አትመልከች ሱፍ" ሙዚቃ በሕዝቡ በኩል ሲደነቅ በመኳንንቱ ወገን ግን በወቅቱ የተካሄደውን የንጉሡን ልጅ ሠርግ ለመንቀፍ ፈልጎ ነው ተብሎ ተነቀፈ፡፡ "ውሻ አሳድጋለሁ" በሚል ርዕስ በ1958 ዓ.ም የተጫወተው ሙዚቃም ተመሳሳይ እጣ እንደገጠመው "ጠመንጃ እና ሙዚቃ" በተሰኘው የይነገር ጌታቸው መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡   

ወታደራዊ የደርግ መንግሥት ሶሻሊዝምን እከተላለሁ ስለሚል ለሕዝብ ማነቃቂያ የሚሆኑ ዘፈኖችን እና መዝሙሮችን ያሠራ ነበር፡፡ ደርግ ለሚያካሂዳቸው ሀገር አቀፍ መርሐ ግብሮች የሕዝብ የማነቃነቂያ ዘፈኖችን ይጠቀም ስለነበር ጥላሁንም በዚሁ መንፈስ “ዕድገት በሕብረት”ን በመሰሉ ኅብረ ዝማሬዎች ላይ መሪ ድምፃዊ ሆኖ ተጫውቷል።

በሶማሊያ ጦርነት ወቅት ጦር ሜዳ ድረስ እየተገኘ የዘፈናቸው ዘፈኖች የሠራዊቱን ወኔ የቀሰቀሱ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች ለጦር ሜዳ የተዘጋጁ ቢሆኑም ጥበባዊ ለዛቸው ግን ግሩም ስለነበር እስከዛሬ እንደ አዲስ ይደመጣሉ። በ1969 የተጫወተው “አጥንቴም ይከስከስ” እንዲሁም በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ ለሕዝብ የቀረበው “ቃል ኪዳን” የተሰኙት ዘፈኖች በዚህ ረገድ የሚታወሱ ናቸው።

በአብዮቱ ዘመን ለአብዮቱ የሠራቸው ብዙ ዜማዎች ቢኖሩም የተጠረጠረባቸው እና እስከመታሰር የደረሰባቸው ጉዳዮችም ነበሩ፡፡ ከተጠረጠረባቸው ጉዳዮች መካከልም ከሀገር ይጠፋል ተብሎ አሜሪካ እንዳይሄድ የተከለከለበት ይገኛል፡፡ መስከረም ወር 1977 ዓ.ም አሜሪካን ሀገር ኮንሰርት እንዲያቀርብ ግብዣ መጣለት። ደስ ብሎት ለመሄድ ሲሰናዳም የአብዮቱ ጠባቂዎች ከሀገር ሊጠፋ ይችላል ብለው ከለከሉት። እንዲያውም ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ለሚኖረው ሥራ እንዲዘጋጅ ሲነገረው አልሄድም ብሎ ራሱን ሰውሮ ሲደበቅ የማዕከላዊ እዝ ባንድ አባላት ያለ እሱ ወደ ቦታው ተጉዘው ሥራቸውን ማቅረብ ጀመሩ። ባንዱ ሥራውን ሲጀምር ግን ታዳሚው “ጥላሁን ጥላሁን” ማለት ጀመረ። እሱ ባለመኖሩ ዝግጅቱ ላይ እንከን እንደፈጠረ የተረዱት የባንዱ ኃላፊዎች ጥላሁንን ከአዲስ አበባ አስገድደው ወስደው በግዴታ አዘፈኑት። አፈሙዝ ተደግኖበት ይዘፍን የነበረው ጥላሁንም ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ራሱን ስቶ ወደቀ። በዚህም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ገብቶ እስከመታከም ደርሶ ነበር።

ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ የሆነው እጣ ፈንታው ሆኖ ከወላጆቹ ጋር የማደግ ዕድል ያላገኘው ጥላሁን፣ ኢትዮጵያን የወላጆቹ ምትክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደግሞ ወንድምና እህቶቹ አድርጎ ስለሚያስብ፣ “የእኔ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” የሚል እምነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይናገር ነበር።

ጥላሁን በ1985 ዓ.ም አንገቱ ላይ ደርሶበት የነበረው አደጋ ድምጹ ላይ እክል ሊፈጥርበት ይችላል ተብሎ ቢታሰብም እንደተፈራው በድምጻዊነት ከመቀጠል አላገደውም።  “ወገን አለኝ”ን ጨምሮ በኋላ በድጋሚ ተጫውቶ ያስቀረጻቸውን ዜማዎች የተጫወተው ከአደጋው በኋላ ነው። “ፍቅርሽ ነው የጎዳኝ” እና “አይ ዘመን” የተሰኙት ዘፈኖችም ከዚሁ ዘመን ሥራዎቹ መካከል ናቸው።

ጥላሁን ከድምጻዊነቱ በተጨማሪም የሚደነቅ የዜማ ደራሲ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ "የጠላሽ ይጠላ"፣ "ስቆ መኖር"፣ "ጎመን በጤና"፣ "ፍቅር ምን ዓይነት ነው"፣ "ቀረች ሳትረዳኝ"፣ "እቱ ስምሽ ማነው"፣ "ምግብማ ሞልቷል"፣ "በቁም ካፈቀርሽኝ"፣ "ምን ጥልቅ አረገኝ" እና "ያቺን ልጅ አትንኩ" የተሰኙ ተወዳጅ ሙዚቃዎች ዜማ የተሠራላቸው በራሱ በጥላሁን ነው፡፡

ይነገር እንደጻፈው መቶ አለቃ ገዛኸኝ ደስታ 42፣ አየለ ማሞ 31፣ ተስፋዬ ለሜሳ 23፣ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ 22 የሙዚቃ ግጥሞችን ለጥላሁን የሰጡ ዋና ዋና የግጥም ደራሲያን ሲሆኑ፣ በጥቅሉ የ18 የሙዚቃ ግጥም ደራሲያንን ሥራዎች ተጠቅሟል፡፡ 13 የዜማ ደራሲያንም በሥራዎቹ እንደተሳተፉ እና ከ13 በላይ የሙዚቃ አለበሞችን ለአድማጮቹ እንዳበረከተ የህይወት ታሪኩ ያሳያል፡፡

በሀገር ፍቅር በተጫወተው “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ” የተጀመረው የጥላሁን የሙዚቃ ህይወት “ቆሜ ልመርቅሽ” በሚለው እና ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ባስቀረፀው የመጨረሻው አልበሙ ነበር የተደመደመው፡፡

ጥላሁን ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እየዘመረ ኖሮ፣ “ሞት እንኳን ጨክኖ ወስዶ ከሚያስቀረው፣

                                                                        ምን አለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው፤…"

በማለት ለሀገር መልካም ለሠሩት ዳግመኛ መፈጠርን ቢመኝም ሞት የተፈጥሮ ህግ ነውና እሱም ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ወደማይቀረው ዓለም ተጓዘ፡፡  ውለታ የማይረሳው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሚያዚያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም በነቂስ አደባባይ ወጥቶ በክብር ሸኘው፡፡

"ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ፣

ይህ ነው የሞትኩኝ ለት የኔ ማስታወሻ፤…"  ብሎ በህይወት እያለ የተናዘዘው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ፣ በኑዛዜው መሰረት ተቀርጾ በተቀመጠው ድምጹ ህያው ሆኖ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ይኖራል፡፡

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top