"የሰው ልጅ በፍትሃዊ ዓለም የመኖር ተስፋው አንድ በአንድ እየሞተ ነው" - ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን

3 Days Ago 150
"የሰው ልጅ በፍትሃዊ ዓለም የመኖር ተስፋው አንድ በአንድ እየሞተ ነው" - ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን

በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም መሪዎች እና ልዑካኖቻቸው በዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ ባለው የግጭት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በጉባኤው ላይ በጋዛ ስላለው ሁኔታ አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ የሰው ልጅ በፍትሃዊ ዓለም የመኖር ተስፋው አንድ በአንድ እየሞተ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እስራኤል በጋዛ እየፈፀመች ያለውን ድርጊት ያወገዙት ፕሬዝዳንቱ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓት እና የምዕራቡ ዓለም እታገልላቸዋለሁ የሚላቸው እሴቶች በጋዛ እየሞቱ ናቸው ብለዋል።

"በጋዛ ህፃናት ብቻ ሳይሆኑ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓትም እየሞተ ነው፣ እውነት እየሞተች ነው፣ ምዕራባውያን እንከላከላለን የሚሉት እሴቶች እየሞቱ ነው፣ የሰው ልጅ በፍትሃዊ ዓለም የመኖር ተስፋ አንድ በአንድ እየሞተ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የዓለም መሪዎች የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እያካሄዱ ያሉትን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጫና ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻውን ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት፣ ረሃብ ለማስወገድ እና የቴክኖሎጂ ሀይልን ለመጠቀም አስተዳደራቸው ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልፀዋል።

አንዳንድ ነገሮች በስልጣን ላይ ከመቆየት የበለጠ አስፈላጊ መሆናቸውን መርሳት የለብንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውና አስፈላጊው ጉዳይ የሰዎች ደህንነት ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በጋዛ ጉዳይ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ የእርዳታ ሰራተኞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነቱ መሞታቸውን ገልፀው፤ እየተባባሰ ያለውን ግጭት በማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት በፍጥነት መከናወን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

"በጋዛ ያለው ስቃይ የሚያበቃበት እና ጦርነቱ የሚያቆምበት ጊዜ አሁን መሆን አለበት" ሲሉም አሳስበዋል።

የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እንዲሁ በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ሰፊ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፤ ደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ ከፀጥታው ምክር ቤት መገለላቸው ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ “ማንንም ወደ ኋላ ሳንተው፤ ለሰላምና እድገት፣ ለዘላቂ ልማት፤ ሰብአዊ ክብር ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ በጋራ እንረባረብ” በሚል መሪ ሃሳብ በኒውዮርክ እየተካሄደ እንደሚገኝ የዘገበው ሲኤንኤን ነው፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top