"መቻዕል ሜራ" (የእብድ ገበያ)

2 Days Ago 233
"መቻዕል ሜራ"  (የእብድ ገበያ)

“መቻዕል ሜራ” የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ ‘ያሆዴ’ በዓል ከሚከበርበት ዕለት ከ15 ቀናት አስቀድሞ የሚጀመርና የበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ ነው።

መቻዕል ሜራ የሚለው ቃል ሀሳቡ የእብድ ገበያ እንደማለት ሲሆን የያሆዴ በዓል አከባበር አንዱ አካል ነው።

ይህ ስርዓት በብሔሩ ባህላዊ አንድምታ ያለውና የገበያ ተጓዦች ስርዓት ሲሆን፤ ከትውልድ ቀያቸው እርቀው የሚኖሩትን የማህበረሰብ አባላት ሳይቀር የሚያገናኝ የበዓል ገበያ ነው።

በዚህ ገበያ ፈጣሪ ይመሰገናል። ሁሉም ሰው ገበያውን ይጎበኛል። በመቻዕል ሜራ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም። ገበያ ገብቶ የለም የሚባል ቃል አይሰማም። ስያሜውም የእብድ ገበያ እንደመሆኑ ከሌሎች የገበያ ቀናት የሚለየው የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎችና ክንዋኔዎች አሉት።

የእብድ ገበያም የሚል ስያሜ ያሰጠው ገበያው የሚደራበት ሰዓት ከወትሮው የተለየ በመሆኑ ነው። የእብድ ገበያ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ እንደመደበኛው ገበያ እስከ ማታ ሳይቆይ ከቀኑ በስድስትና በሰባት ሰዓት ሰው ተገበያይቶ ገበያው ይበተናል።

መቻዕል ሜራ የሀዲያ አባቶች "ጊዜውን እንዴት እንጠቀም" በሚል በባህላዊ ጥበብ የተቀነባበረ የጊዜ አጠቃቀምን የሚያሳይ ሲሆን፤ በዚህ ገበያ አባወራ ከቀረቡ ሰንጋዎች መካከል መርጦ ቀልቡ ያረፈበትን ሙሉ ብር እንኳን ባይኖረው ገዝቶ የሚወስድበት የግብይት ሥርዓት ነው።

ምንም ብር ከሌለው ደግሞ ከመጣበት አካባቢ የአንዱን ታዋቂ ሰው ስም በመጥራት ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ያለ ምንም ተያዥ ይዞ ይሄዳል። ቀሪውን ብር ደግሞ በአዝመራ ወቅት ይከፍላል።

በዚህም መሰረት አባወራዎች ለያሆዴ የወሰዱትን ሰንጋ ከህዳር እስከ ጥር ባለው ወራት ውስጥ በታማኝነት ከፍለው ያጠናቅቃሉ። በዕብድ ገበያ እናቶች ለያሆዴ በዓል አተካና ለማዘጋጀት የሚጠቅሙ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የእንሰት ተዋፅኦ ያዘጋጀሉ።

በዚህ ቀን የማይሸመት ነገር የለም። ለበዓሉ ድምቀት አስፈላጊው ነገር ሁሉ ይገዛል ….ሁሉም የበዓሉን ቀን ለማሳመር የሚገኝበት አስደናቂው የመጨረሻው የቅዳሜ ገበያ መቻዕል ሜራ (የእብድ ገበያ) የያሆዴ ድምቀት።

በናርዶስ አዳነ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top