በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ለቱሪዝም እድገት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

1 Day Ago 142
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ለቱሪዝም እድገት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ከቅርብ አመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም እድገት ሰፊ ትኩረት ሰጥታ እየሰራችበት ትገኛለች፡፡

እነዚህ የሚገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች እና መስህቦች ለሀገሪቷ ሰፊ የኢኮኖሚ ዋልታም ሆነዋታል፡፡

ለጎብኝዎች ምቹ ያልነበሩ ቦታዎችን በማስተካከል እና በመገንባት ከቱሪስቱ አልፈው ለነዋሪውም ተጠቃሚ የሚሆኑበት አግባቦች ተፈጥረዋል፡፡

በክልሎች እየተገነቡ እና እየታደሱ ያሉ እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ ያሉ መስህቦች ለሀገሪቱ ሌላ የገቢ ምንጭ ሆነዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ በክልሎች ላይ ያለው አስተዋጽኦ በሚመለከት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢፈባስ አብዱልዋሀብ ለኢቲቪ እንደገለፁት፤ በክልሉ ለቱሪዝሙ እድገት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

በክልሉ ወደ 24 ፓርኮች እና ወደ 18 የሚጠጉ ኢኮ ቱሪዝም ሳይቶች እንደ አዲስ መገንባታቸውንም ገልፀዋል፡፡

42 አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውንም የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም ክልሉ እንዳለው የተፈጥሮ ሀብት አለመስራቱንና አሁን ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰቶት እንተሰራበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ያነሱም ሲሆን ለትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ጥሪ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ የተለያዩ ባህልን የሚያስተዋውቁ ስራዎች መሰራታቸው አንስተው፤ በክረምት ወራት እንደ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እግጫ ነቀላ ያሉ በዓላት በድምቀት መከበራቸውን ተናግረዋል፡፡

የመስከረም ወር በክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ወር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ 13 ቅርሶች መካከል 3ቱ በአማራ ክልል እንደሚገኝ የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው፤ እነዚህን ቅርሶች በመጠበቅ እና ለቱሪዝም ምቹ እንዲሆኑ እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መጪውን የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top