ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

2 Days Ago 97
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2017 ዓመት የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓሉ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

የመስቀል በዓል የሕልም ጉልበት የታየበት በዓል ነው፡፡

ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ያለመችው ምንም አመቺ ነገር ባልነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ዙሪያዋ ጨለማ ነበር፡፡ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ፡፡ ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ማንም በማያስበው ጊዜ፤ አይቻልም አይሞከርም በሚባልበት ወቅት፤ አንድ ቀን፤ ፈጣሪዋ ሲፈቅድ፤ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት ሕልም ነበራት፡፡

ሕልሟ እንዲሳካ ሠራች፤ ታገለች፡፡ ጨለማውን እየገፈፈች፤ አስቸጋሪውን ጎዳና እየጠረገች፤ ከውስብስብ ችግሮች ጋር እየተጋፈጠች ወደ ፊት ተጓዘች፡፡ በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ተሻግራ፣ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት በቃች፡፡ ሕልሟ እውን ሆነ፡፡ ታሪክን ቀየረች፡፡ ልዕልናን ዐወጀች፡፡ ደመራ ለሚታገል፤ ተስፋ ለማይቆርጥና እስከ መጨረሻው ለሚጸና ሰው ሕልሙ አንድ ቀን እውን እንደሚሆን የሚያሳይ ትእምርት ነው፡፡

እዮሃ፤ ማለት “ይሄዋ” ማለት ነው ይባላል፡፡

ይሄው ተገኘ፤ ይሄው ተሳካ፤ ይሄው እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ ከበረቱ፤ ከታገሉና ከጸኑ የማይሳካ ምን ነገር አለ? ሕልሙን ለሚያውቅ፤ ሕልሙ እንዲሳካ በነገሮች ተስፋ ሳይቆርጥ ለሚለፋ፤ እንደ ንግሥት እሌኒ ሕልሙ እውን ሆኖ አንድ ቀን ማየቱ አይቀርም፡፡ የሕልሙን ደመራ መደመሩ አይቀርም፡፡ “እዮሃ”፤ “ይሄዋ!” ማለቱ አይቀርም፡፡

መስቀል ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሁለት መንገድ የሚያሳይ በዓል ነው፡፡ ደመራው ከእንጨት ወደ ችቦ፤ ከችቦ ወደ ደመራ የሚያድግበት መንገድ መደመር ምን ያህል ኃይልና ጉልበት እንዳለው ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መስቀል በተለያየ መንገድ፣ በተለያየ ባህልና አከባበር በብዙ ብሔረሰቦች ይከበራል፡፡ ይሄ ደግሞ በኅብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን ነባር ትሥሥር፣ የወል ትርክትና አንድነት የሚሳይ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት በዓላት ሃይማኖታውያን ብቻ አይደሉም፡፡ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫዎች ጭምር ናቸው፡፡ በመደመር ውስጥ ያለውን ጥንካሬና ጉልበት የሚሳዩ ትውልድ ለእኛ ትምህርት ያቆማቸው ምልክቶች ናቸው፡፡

ደመራውን በደመርን ጊዜ፤ ደመራውን በለኮስን ጊዜ፤ እንደየባህላችን የመስቀልን በዓል ለማክበር በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ በተሰባሰብን ጊዜ ኢትዮጵያን እናስባት፡፡

የሁላችንም ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ወጎች፣ ዐቅሞች፣ ጸጋዎች፣ ሀብቶች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች፣ ወዘተ. ተደምረው ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና የተከበረች ሊያደርጓት እንደሚችሉ እናስብ፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ድምር መሆኗን እናስብ፡፡ ከድምሩም በላይ መሆኗንም እናስብ፡፡ ደመራውን እያሳየን ለልጆቻችን ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉሙ በተጨማሪ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደደመራው ከፍ ብለን እናበራለን” በሏቸው፡፡

መልካም የመስቀል በዓል ይሁን፡፡   

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 16፣ 2017 ዓ.ም


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top