“የዶሮ እንቁላል አለ”

3 Days Ago 141
“የዶሮ እንቁላል አለ”

ሆሳዕና ጎዳናዎች ላይ እሚያዘወትር ማነኛውም ሰው ያውቀዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ሳቂታ ነው፣ ኑሮ ቢከብደው እጅ ያለሰጠ እንደውም ከመንግስት ስራው ጎን ለጎን እንቁላልና የሞባይል ካርድ የሚነግድ ተግቶ የሚያተጋ ጀግና ነው ይባልለታል።

የመሰረተ ልማት ግንባታ በሰፊው በሚከወንባት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከተማ በሆነችው የሆሳዕና ከተማ አቧራ እና ፀሀይ ሳይበግረው ፈገግ እያለ ኑሮውን የሚገፋ ኑሮ አሸንፎ ያላንበረከከው ትጉህ ወጣት ብርሃኑ ተሻለ።

በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ጽ/ቤት የገቢ ምጣኔ ጥናትና መመሪያ ዝግጅት የስራ ዘርፍ ላይ በባለሙያነት ህዝቡን የሚያገለግል የመንግስት ሰራተኛም ነው።

ለሀድያ ዘመን መለወጫ ያሆዴ ወደ ሆሳዕና ባቀናንበት ወቅት ነበረ  በቅዳሜ ቀን እንቁላል ሱቅ ጋር እንቁላል ሊረከብ  ሲጠብቅ ያገኘነው።

ብርሃኑ ተሻለ የተወለደው በሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ አሼ ቡቁና ቀበሌ ነው፡፡ የእሱ ቤተሰብ ካፈራቸው 5 ልጆች 3ኛና ብቸኛ ወንድ ልጅም ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ከሆሳዕና ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አሼ ቡቁና ቀበሌ ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በየካቲት 25/67 ት/ቤት እና የመሰናዶ ትምህርቱን በዋቸሞ መሰናዶ ት/ቤት ተምሮ አጠናቋል።

የገጠር ልጅ ነኝና እነዚህን ትምህርት ክፍሎች ስማር የተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሁኜ አልነበረም የሚለው ብርሃኑ በእግሩ ከመጓዝ ጀምሮ ቤት ተከራይቶ እስከመማር ሁሉንም አይቶታል።

በዚህ የሕይወት ጉዞው ላይ ተርቧል፣ ተጠምቷል ግን አላማው ትልቅ ነበረ። መማር፣ እራሱን መለወጥ፣ ቤተሰቡን ማገዝ ለዚህም ጠንክሮ ተምሮ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ በመጀመርያ ዲግሪ ለመመረቅ በቃ።

ከዚያም በ2006 ዓ.ም አሁን እየሰራ በሚገኝበት የሆሳዕና ከተማ ገቢዎች አስተዳደርን ተቀላቅሎ በመስራት ላይ ይገኛል።

ተምሮ የተሻለ ሕይወት መኖርን ህልሙ ያደርገው ብርሃኑ ተሻለ በመንግስት ስራው ብቻ ህልሙን መኖር እንደማይችል ሲረዳ ቁጭ ማለትን አልመረጠም። ተጨማሪ ገንዘብ ምንጭ እንዲኖረው ከማሰብ አልፎ የሚሰራውን ማሰላሰል ጀምሯል።

እናም አስቦ ከመንግስት ስራው ጎን ለጎን ብርሃኑ ያለውን ትርፍ ሰዓት ሌላ ስራ ለመስራት ወሰነ።

ይህን ውሳኔ ሲወስን ግን ያ የቢሮ ሰራተኛው ብርሃኑ ወደ ጭንቅላቱ የመጣው  እንደ ሳሙናና እስኪብርቶ ያሉ ትናንሽ ሸቀጦችን ከስራ በኋላ እያዞሩ መሸጥ ነበረ።

አዎ ልብሱን በሥነ-ስርዓት ለብሶ ቆሻሻ ሳይነካው በመንግስት መስሪያቤት የሚውለው ብርሃኑ ዝቅ ብሎ ደግሞ በ2007 ዓ.ም በትርፍ ሰዓቱ እስኪብርቶና ሳሙና ሽያጭ ስራውን ጀመረ።

ብርሀኑ በዚህ አላቆመም ከአንድ ጓደኛው ጋር በመምከር እንቁላል ከገበሬ ይረከባሉ ከተማ አምጥተው መሸጥ ጀመሩ።

ነገር ግን በመሀል በጋራ ከጓደኛው ጋር የተጀመረው ንግድ ኪሳራ አጋጠመውና ሱቃቸው ተዘጋ።

በዚህ ጊዜ ለነገ የተሻለ ነገር ይኖረኛል ብሎ ባለችው ትርፍ ሰዓት ወደ ስራ ተሰማርቶ የነበረው ብርሀኑ ተስፋ አልቆረጠም። እንቁላል እየተሸከመ ወደ መሸጥ ተሸጋገረ እንጂ።

እንደቀድሞው በብዛት ከገበሬ ባይረከብም ከከተማ አስረካቢዎች በቁጥር  እየተረከበ መስራቱን ግን ተያያዘው።

ብዙ ሰው የመንግስት ወይም የግል ተቀጣሪ አይደፍረውም የሚባለውን የጎዳና ንግድ ከቢሮ ተመልሶ ልብሱን ቀይሮ መሸጡን ተያያዘው።

ዛሬ እሱን በሆሳዕና ከተማ ውስጥ የማያውቀው የለም። ብርሃኑ ተብሎ ስሙ ሲነሳ “የዶሮ እንቁላል አለ” የሚለው ልጅ መለያው ሆኗል።

ከደረቱ “የሞባይል ካርድ አለ” የሚል ታፔላ የያዘውና የእንቁላል ካርቶን ተሸክሞ ፈገግ የሚለው ብርሃኑ ነገ የተሻለ ነው ብሎ ያምናል።

ሰው ከለፋና በጊዜ ሂደት ካመነ ለውጥ ያመጣልም የሚለው ብርሃኑ ስራውን ሲጀምር ብዙዎች ነቅፈውታል። ይህ ብቻም አይደለም ገቢዎች ስለሚሰራ ነው እድሉን የተጠቀመው ብለውም ወቅሰውታል። አይ የመንግስት ስራ ሰዓት ቢበድልስ ሲሉ በጥርጣሬ አይን ያዩትም ብዙ ናቸው። ያለኝን ይባርክልኝ ብሎስ አይኖርም ብለው የተናደዱበትም አልጠፉም።

እሱ ግን በጎውንም ጥሩውንም ወሬ እየሰማ በትዕግስት ስራውን ቀጠለ። እናም ብርሃኑ የ30ቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደፋር እና ትሁት ስራ ወዳድ ወጣት እንደሆነ ብዙ የከተማው ሰዎች ዛሬ ላይ ይመሰክሩለታል። ኑሮን ለማሸነፍ በሄደበት መንገድ ብዙሃኑ ይደነቃሉ።

ሰው ያበረታዋል አይዞህ ይለዋል። እሱም በስራው ደስተኛ ነው “ከተሰጠኝ የመንግስት ሀላፊነት ሳላጓድል እየሰራሁ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ አግኝቻለሁ” የሚለው ብርሃኑ “ድህነት እንጂ ስራ አያስንቅም ደግሞም አይናቅምም” ሲል ለኢቢሲ ሳይበር  ተሞክሮውን አጫውቷል።

ብርሃኑ በመንግስት ስራ የማገኘው ደሞዜ ለመኖር በቂ ቢሆንም ፍላጎቴን ገድቤ ነበር የምኖረው አሁን ግን ተጨማሪ የገቢ ምንጭም በመኖሩ በጥሩ ሁኔታ ቤተሰቤን እያስተዳደርኩ ፍላጎቴን አሟልቼ ነው የምኖረው ሲል በፈገግታ ተሞልቶ ነው።

የከተማው ሰው “እንቁላል የማያስወድደው ልጅ” ሲሉት ሰምተን ብንጠይቀው አዎ እኔ ለብዙ ትርፍ አልሰራም ለረጅም ጊዜ መስራቱ ይበልጥብኛል ሲል ነበረ የመለሰልን።

ስራን ስናከብረው ያስከብረናል የሚል መርህ ያለው ብርሃኑ በግለሰብ ደረጃ ዝቅ ብለን እና ሥራ ሳንመርጥ ከሰራን የግል ፍልጎታችንን ከማሟላትም ባለፈ እንደ ሀገር ለመለወጥም እድላችን ሰፊ ነው ሲል በብሩህ ፈገግታ እና ተስፋ ነው።

ዛሬ ላይ ሳይሳቀቅ ቤተሰቡን እየመራ ፍላጎቱን እና ፍላጎታቸውን ሳይገድብ የሚፈልገውን ሁሉ ማሟላት የቻለው ብርሃኑ በሂደት እንኳን እኛ በሀገር ደረጃም መለወጥ እንደምንችል ይህ ምልክት ነው ባይ ነው።

 “ስራ ክቡር ነው”

ስራሽን ስሪ

ስራህን ስራ” የሚለው ስንኝ  በትክክል የሚሰራው ለእንደብርሃኑ ላሉ ዝቅብለው ሰርተው ነገን ከፍ ለማለት ለሚጥሩ ወጣቶች ነውና እኛም ስራ ክቡር ነው እንላለን።

በናርዶስ አዳነ

ካሜራ አሰግድ ሲሳይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top