ሊባኖስ የሀሰን ናስራላህ ሞት ተከትሎ የ3 ቀን ብሔራዊ ሃዘን አወጀች

4 Days Ago 157
ሊባኖስ የሀሰን ናስራላህ ሞት ተከትሎ የ3 ቀን ብሔራዊ ሃዘን አወጀች

ሊባኖስ የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ሞት ተከትሎ የሶስት ቀናት ብሄራዊ ሃዘን ማወጇ ተሰምቷል።

የሃገሪቱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ በትናትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ የሀሰን ናስራላህ ሞት ተከትሎ ሃገሪቱ ያወጀችው ብሄራዊ ሀዘን ሰኞ እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡

ሂዝቦላህ የሀሰን ናስራላህ የቀብር ስነ ስርዓት የሚፈፀምበትን ቀን እስካሁን ባያሳውቅም፤ በናስራላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቀን የመንግስት ተቋማት ዝግ ሆነው እንደሚቆዩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እስራኤል አርብ እለት በቤሩት በፈፀመችው ከባድ የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ  መሪ ሀሰን ናስራላህ መገደላቸውን ሄዝቦላህ ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

ግድያው የተፈፀመው የሂዝቦላህ አመራሮች በዳሂየህ በሚገኘው ዋና ፅህፈት ቤታቸው ሰብሳባ ላይ በነበሩበት ወቅት በተሰነዘረ የአየር ጥቃት መሆኑም ተጠቅሷል።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየፈጸመች ያለውን የአየር ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏ የተገለፀ ሲሆን፤ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ባካሄደችው የአየር ድብደባ 15 ሰዎች መገደለቻው ተገልጿል፡፡

ባለፉት ቀናት እስራኤል በሊባኖስ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ከ720 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

የእስራኤል ጥቃት በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ስጋትን እና ውጥረትን የፈጠረ ሲሆን፤ በደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top