በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የመስጠቱ አንድምታ

3 Days Ago 452
በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የመስጠቱ አንድምታ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ምልክት ነው። አየር መንገዱ ንብረትነቱ የመንግሥት ሲሆን፣ አስተዳደሩ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ ተቋም ነው፡፡ 78ኛ ዓመቱን ያከበረው አየር መንገዱ የተቋቋመው ታኅሣሥ 12 ቀን 1938 ዓ.ም ሲሆን፣ ሥራውን በይፋ የጀመረው መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ነው፡፡

በአምስት C-47 አውሮፕላኖች ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመጀመሪያ በረራውን ያደረገው በአስመራ በኩል ወደ ካይሮ ነበር፡፡ አየር መንገዱ ዛሬ B767፣ B777-200LR፣ B787 ዲሪምላይነር አውሮፕላኖችን እንዲሁም ቦይንግ 787-9 ጨምሮ አዳዲስ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችን ወደ አፍሪካ በማስገባት ረገድ ቀዳሚ ነው። Airbus A350 XWBን ሥራ ላይ በማዋልም የመጀመሪያው ነው፡፡ 

 

ላለፉት 78 ዓመታት በማንኛውም ወጀብ ሳይናወጥ የቆየው አየር መንገዱ ኢትዮጵያ ውስጥ በስኬታማነት ከቀጠሉት ምርጥ ተቋማት መካከል ግንበር ቀደሙ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ውጤታማ፣ ትርፋማ እና ተሸላሚ እየሆነ የቀጠለው መሰረት ያለው ተቋም በመሆኑ ነው፡፡በአፍሪካ ደረጃ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት እና በተቋማዊ መሰረቱ ግንበር ቀደም ነው።

የዓለም አቀፍ የአየር መንገዶች ጥምረት የሆነው የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአህጉሪቱ ትልቁ አየር መንገድም ነው። የ146 አውሮፕላኖች ባለቤትም ነው፡፡ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አየር መንገዱን ሲመሰርቱ ኢትዮጵያን ለማዘመን ሲሆን፣ አየር መንገዱም የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ አድርሶ ግዙፍ ተቋምነቱን አስመስክሯል። ከዋና ዋና ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ጋር በተባባሪነት እየሠራ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ 136 የተሳፋሪዎች እና 68 የጭነት መዳረሻዎች አሉት። በዚም ‘አፍሪካን ከማገናኘት ባሻገር’ ብሎ የተነሳበትን ዓላማ በስኬት እየተወጣው ይገኛል፡፡

በዚህ ስኬቱም ባለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ 25 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። የ2025 የ15 ዓመት ስትራቴጅክ እቅዱን ቀድሞ ያሳካው አየር መንገዱ፣ ዕድገቱን ይበልጥ ለማጠናከር "ቪዥን 2035" የተሰኘ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ስኬታማ ጉዞውን ቀጥሏል።

ይህን ግዙፍ ስም ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ሥራ የማስኬድ ተግባር እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህን ሎጆች የሚያስተዳድረው በስካይ ላይት ሆቴል በኩል እንዲሆንም የስምምነት ተፈራርሟል።

አየር መንገዱ እንዲያስተዳድራቸው ከተሰጡት በገበታ ለሀገር ከለሙት ሎጆች መካከል ጎርጎራ፣ ሃላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ አገልግሎት ጀምረዋል።

ስካይ ላይት ሆቴል የአየር መንገዱን እንግዶች ቆይታ ለማራዘም ታስቦ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ባለ አምስት ኮከብ ቅንጡ ሆቴል ነው፡፡ ሆቴሉ በግልም ሆነ በድርጅት ለሚጓዙ ደንበኞቹ ለመዝናኛም ሆነ ለማንኛውም ቆይታ የሚመች ኢትዮጵያዊ መስተንግዶን ከዓለም አቀፍ ደረጃ መስተንግዶ ጋር አጣምሮ እንግዶቹን አያገለገለ ያለ ሆቴል ነው፡፡

በዚህ ላይ እነዚህ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ እይታ ከፍ ያደርጋሉ ተብለው የተገነቡት ሎጆች ሲጨመሩለት አየር መንገዱ ለእንግዶቹ የሚያደርገውን መስተንግዶ ከፍ ያደርጉታል፡፡ በተለይም የተፈጥሮ አድናቂ ተጓዦች ለሚያደርጉት ቆይታ የተመቸ ሁኔታን በመፍጠር ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ እና የኢትዮጵያን ገጽታ የማሳመር ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

አየር መንገዱ ካሉት ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን እና በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፉ እንግዶቹን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የቱሪዝም ዘርፉን ያሳድጋል፡፡ እንኳን ስራው ስሙ ብቻ የሚያኮራው እና መለያ የሆነው አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ደንበኞቹ እነዚህን ቦታዎች ለመጎብኘት ፍላጎታቸው እንዲጨምርም ያደርጋል፡፡

አየር መንገዱ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በላይ ያካበተውን ተቋምን በውጤታማነት የመምራት አቅሙን ተጠቅሞ እነዚህን ሎጆች ለታለመላቸው ዓላማ ያውላቸዋል ተብሎም ይታመናል፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top