ፖሊስ ከየትኛውም ሐይማኖት፣ ብሔር እና ፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ እና ብዝኀነትን እሴቱ ያደረገ ሕዝባዊ ተቋም መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሐይማኖቶች ብዝኀነትን የሚያከብርና የሚያስከብር በእኩልነት ለሁሉም ሙያዊ አገልግሎት የእየሰጠ ያለ ተቋም እንደሆነ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል።
ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ አዲስ የፖሊስ አባላትን ለመመልመል ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የተላከ የፖሊስ አባል ምክትል ሳጂን ታመነ ዱባለ፤ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ኬቾ ወዜ ቅዱስ ባለወልድ ቤተክርስቲያን በመገኘት የደንብ ልብሱን እንደለበሰ ሐይማኖታዊ መዝሙር በመዘመር እና በሕዝብ ፊት ጥይት እየተኮሰ የሚያሳየው በማህበራዊ ሚዲያ ሰሞኑን እየተሰራጨ ያለው ቪዲዮ ከተቋሙ መተዳደሪያ ሕግና አሠራር ውጭ እንደሆነ የፌደራል ፖሊስ አረጋግጧል።
አባሉም ይህንን ተግባር እንደፈፀመ ወዲያውኑ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎት የፈፀመው ድርጊት በተቋሙ ሕገ ደንብ መሠረት በሕግ አግባብ እያጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ በመግለጫው አመላክቷል።
ፖሊስ የሁሉም አገልጋይ ሆኖ ሳላ አባሉ እምነቱን በግል መከተል እየቻለ፤ ነገር ግን መንግስት ፀጥታ እንዲያስከብር ያስታጠቀውን የጦር መሣሪያ ከፍተኛ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ፍፁም የፖሊስን ዲሲፕሊን በጣሰ መልኩ የፈፀመው ተግባር በሕግ የሚያስጠይቅ ስለሆነ ተቋሙ ሕግ ፊት እንደሚያቀርበው ገልጿል።
አባሉ የፈፀመው ተግባር እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ ከዚህ ውጭ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚራገቡ የተሳሰቱ መረጃዎችን ኅብረተሰቡ እንዳይከተል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለመገናኛ ብዙኀን በላከው መግለጫ አሳስቧል።