ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

13 Days Ago
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።
 
አገልግሎቱ “ሀገራዊ መግባባት እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና” በሚል ርዕስ ለኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በሥልጠና መርሐ ግብሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረታቸዉ በመረዳት የሰላም ግንባታ ሂደቱን ለማፋጠን የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
 
ሥልጠናው ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት፣ ከዞንና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከየፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ከፍኛ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው፡፡
 
በሥልጠናው የመጀመሪያ ቀን ውሎ “የገዥ ትርክት ግንባታ እና የኮሙኒኬሽን ሚና” በሚል ርእስ የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ገለጻ አቅርበዋል፡፡
 
ገዥ ትርክት የሀገር አንድነት መሠረት መሆኑን ያመላከቱት አቶ አዲሱ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትርክቱን በመትከልና በማጽናት ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
 
የሥልጠናው ዓላማ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን በሥልጠና በማገዝ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ፣ የተናበበ እና የተቀናጀ መረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ሚዲያን በአጀንዳ ለመምራት ዐቅም ለመፍጠር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ተሳታፊዎች እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመረዳት የሀገረ መንግሥት ግንባታውን በኮሙኒኬሽን ለመደገፍ፣ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ በፍጥነትና በጥራት ለመስጠት እንደሚጠቅማቸው ጠቁመዋል፡፡
 
በዛሬው ሥልጠና 200 የሚደርሱ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከአገልግሎቱ ማኅበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በትኩረት እየሠራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል የዘርፉን የሰው ኃይል ዐቅም መገንባት አንዱ መሆኑን አስታውቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top