በተሻሻለው ደንብ 50/2015 እንደተደነገገው፤ ማስቲካ መንገድ ላይ ከመጣል ጀምሮ ቆሻሻን በየቦታው መጣል ጋር በተያያዘ ሕግ ወጥቷል።
አዲስ አበባ ከሌሊት 10፡00 ሰዓት ጀምሮ በቀን ውስጥ ሦስት ጊዜ በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ንፅህናዋ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ብዙ ሐብት እየወጣ ከተማዋ መሆን በሚገባት ልክ ንጹህ ከተማ አለመሆኗ ጥያቄን ይፈጥራል።
በእርግጥ በተሳሳተ የቆሻሻ አወጋገድ ምክንያት የቆሸሹ ስፍራዎችን በከተማዋ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።
በአዲስ አበባ በመንገድ ጽዳት ስራ ላይ የተሰማሩ ወ/ሮ አይሻ ሀሰን ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በቀን ሦስት ጊዜ እንደሚያጸዱ ገልጸው ፤ በስራቸው ሂደት ውስጥ ግን ብዙ እክሎች እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
እንደ ወ/ሮ አይሻ ሃሳብ፤ የነዋሪዎች የቆሻሻ አወጋገድ ልምድ ግዴለሽነት ያለው መሆኑ እና የፕላስቲክ ጠርሙሶች ለመልቀም ሲባል የተሰበሰቡ ቆሻሻዎች መበታተን ሁሌም የሚገጥማቸው ችግር ነው።
በሕገወጥ የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቆሻሻዎችን በየመንገዱ ጥለው መሄዳቸው አንዱ ችግር ነው የሚሉት ሌላኛው የመንገድ ጽዳት ባለሞያው አቶ አስቻለው ከበደ፤ እንደዚህ በቀን ሦስት ጊዜ ባይጸዳ ከተማዋ ምን ልትመስል እንደምትችል ይጠይቃሉ።
ዋናው የንጽህና ጉድለት የነዋሪዎች ግንዛቤ እጥረት እንደሆነ በመግለጽ፤ ለህብረተሰቡ "የቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ ግንዛቤ እና አስተማሪ ቅጣት"ሊኖር እንደሚገባም ነው አቶ አስቻለው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ፤ በከተማዋ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን የሚሰጡ ባለሙያዎች ስለመኖራቸው አስታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር)፤ ህብረተሰቡ የከተማዋን ንፅህና እንዲጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች እየተሰጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ዋናው ነገር ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ባህሉን ማሳደግ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቆሻሻን በተገቢ ቦታዎች ማስወገድ እንደሚገባ በሕጉ ጭምር አስገዳጅነት አንዳለው አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ፤ ሕጉን የማያከብሩ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ እና አስተማሪ ስራዎችን በመስራት በኩል ውጤታማ ስራ አለመሰራቱን ተናግረዋል።
በተሻሻለው ደንብ 50/2015 እንደተደነገገው ማስቲካ መንገድ ላይ ከመጣል አንስቶ ቆሻሻን በየቦታው መጣል ጋር በተያያዘ በሕግ እንደተደነገገ ዋና ዳይሬክተሩ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) አመላክተዋል።