በየዓመቱ በጎርጎሳዉያን የዘመን ቀመር ሚያዝያ 30 ዓለም አቀፍ የጃዝ ቀን ይከብራል፡፡ ይህ ቀን የጃዝ ሙዚቃን ጥበብ እና ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖን ለማጉላት የሚከበርብት ነው፡፡
ዕለቱ እ.ኤ.አ. በ2011 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተወሰነ ሲሆን በዝነኛዉ የጃዝ ፒያኖ ተጫዋች እና የዩኔስኮ በጎ ፈቃድ አምባሳደር ሄርቢ ሃንኮክ አስተባባሪነት የሚመራ ዓለም አቀፍ ቀን ነዉ።
ቀኑ ሲከበር ዓለም አቀፉን የጃዝ ስልት ኢትዮጵያዊ በማድረግ ታላቅ አሻራዉን ያሳረፈ የሙዚቃ ፈርጥ ክቡር ዶክተር አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ አለማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
ዛሬ ዓለም አቀፍ የጃዝ ቀን እንደመሆኑ የጃዝ ሙዚቃን ከሀገር በቀል ዜማዎችና መሳሪያዎች ጋር በማጣመር ውብ ዜማን ስለፈጠረው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ስራዎች ለማስታወስ ወደድን፡፡
አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እ.አ.አ በ1943 በጅማ የተወለደ ሲሆን በሙዚቃዉ ዓለም እውነተኛ ተምሳሌት የሆነ የሙዚቃ ባለሙያ ነዉ። የኢትዮጵያን ሙዚቃዊ ወጎች ከጃዝ፣ ፈንክ፣ የላቲን ሪትሞች እና የራሱ አሻራ ያረፈባቸዉ የስለተ ምት ዜማ የሚያወጣ የሙዚቃ መሳሪያ ጋር በማዋሃድ "የኢትዮ-ጃዝ አባት" በመባል በሰፊው ይታወቃል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወለድም የሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ጉዞ ከባህር ማዶ የተጀመረ ነዉ። በመጀመሪያ ከጃዝ እና ከላቲን ሙዚቃ የተዋወቀበት አጋጣሚ ዌልስ ውስጥ የኤሮኖቲካል ምህንድስናን በሚማርበት ወቅት ነዉ። ይህ ወቅት ህይወቱን ወደ ተለየ አቅጣጫ የሚወስድ ስሜት የቀሰቀሰበት ነዉ።
በኋላም በለንደን እና በኒውዮርክ ከተሞች የሙዚቃ ትምህርትን ተከታትሏል፣ ክህሎቶቹንም በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ማለትም በቫይብራፎን፣ ኮንጋስ እና ኪቦርዶች አዳብሯል።
እ.አ.አ በ1970ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም፣ ሙላቱ አዲሱን የሙዚቃ እውቀቱን ለትውልድ ሀገሩ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ለማካፈል በከፍተኛ ጉጉት ነበር የመጣዉ። ሆኖም፣ የምዕራባውያንን የጃዝ ዘይቤዎችን በመድገም እንደነበረ ለማካፈል ብቻ አይደለም ያሰበዉ፤ ጃዝን የተለየ ኢትዮጵያዊ የሆነ ድምጽ ለመፍጠር ነበር የፈለገዉ።
ሙላቱ የኢትዮጵያን ባህላዊ የፔንታቶኒክ ስኬሎች፣ ማለትም እንደ “ትዘታ” ያሉ ውስብስብ ዜማዎችን እና ነፍስን የሚያድሱ ድምጾችን በቅንብሮቹ ውስጥ በማካተት ነዉ የተማረዉን የሙዚቃ ትምህርት ሀገር በቀል ለማድረግ አቅዶ የተገበረዉ።
አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሙዚቃ መሳሪያዎች ዉስጥ የማይታዩ እንደ ቫይቫ ፎን እና ኮንጋስ ያሉ መሳሪያዎችን አስተዋውቋል፣ ይህም ደማቅ እና ልዩ የሆነ የድምፅ መሳሪያን ብዝሃነት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ የፈጠረ ነዉ።
እ.አ.አ 1970ዎቹ የኢትዮ-ጃዝ ሙዚቃ ማበብ የታየበት ወቅት ነበር። እነሱም “ሙላቱ ዘ ኢትዮጵያ” (1972) እና “የካቲት ኢትዮ ጃዝ” (1974) ያሉ የሙላቱ አልበሞች ተመልካቾችን በመማረክ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን እንዲሆኑ የሚጠቀሱ ናቸዉ።
በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የፊልም ዳይሬክተር ጂም ጃርሙሽ በኢትዮ-ጃዝ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየቱ የኢትዮ-ጃዝ ማራኪ ድምጾችን አዲሱን ትውልድ ለማስተዋወቅ የሙላቱ አስታጥቄ ሙዚቃን በ‹‹Broken Flowers›› በተሰኘዉ ፊልሙ ላይ ተጠቅሞታል፡፡
በመክብብ ተዘራ