በሁዋዌ አይሲቲ የክፍለ አህጉራዊ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ

1 Mon Ago
በሁዋዌ አይሲቲ የክፍለ አህጉራዊ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ

በቱኒዚያ በተካሄደው የሁዋዌ አይሲቲ የክፍለ አህጉራዊ ፍፃሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል።

ኢትዮጵያን ወክለው በኮምፒውቲንግ ትራክ (Computing Truck) የተወዳደሩት የሦስት ተማሪዎች ቡድን ሞሮኮ እና ቱኒዚያን ተከትለው 3ኛ ደረጃን ማግኘታቸው ተገልጿል።

የፍጻሜ ውድድሩ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሄደ ስለመሆኑ ተገልጿል።

3ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ተማሪዎች ሁለቱ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም አንዱ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።

ኩባንያው ለተማሪዎቻቸው ድጋፍ ላደረጉ መምህራንም ዕውቅና መስጠቱም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በ3 ቡድኖች በተከፋፈሉ በ9 ተማሪዎች ተወክላ የነበረ ሲሆን፤ በ3 የተለያዩ ምድቦች፡ ክላውድ ትራክ፣ ኮምፒውቲንግ ትራክ እና የኔትወርክ ትራክ ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆኑት ተማሪዎች በ2024 በቻይና በሚካሄደው እና ከ500 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሚሳተፉበት የመጨረሻው ምዕራፍ ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድል ይኖራቸዋል ተብሏል።

በቱኒዚያ በተካሄደው ውድድር ከኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ እና ሞሮኮ የተውጣጡ 90 ተማሪዎች በተለያየ የውድድር ዘርፍ ተሳታፊ ሆነዋል።

የሁዋዌ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሊሚንግ ዬ ኩባንያው ተማሪዎች የአይሲቲ ዕውቀታቸውን እና የተግባር ክህሎታቸውን የሚያጎለብቱበትን መድረክ ማመቻቸቱን ገልጸው፤ ይህም ተማሪዎች የፈጠራ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ለዓለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተነደፈ የአይሲቲ ክህሎት ማሳደጊያና ማበልጸጊያ መድረክ ነው።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top