የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች የውይይት መድረክ የአቋም መግለጫ

1 Mon Ago
የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች የውይይት መድረክ የአቋም መግለጫ

ቃላችንን እናከብራለን! በዘላቂነት እግር እንተክላለን!

እኛ የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም በክልላችን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት፤ በእውነት እና በእውቀት የመከርንበትን የውይይት መድረክ በክልላችን ርእሰ-መዲና በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ አካሂደናል፡፡

የውይይት መድረካችን የክልላችንን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት የገመገመ እና የምንገኝበትን ተጨባጭ ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ መነሻ ሰነድ ቀርቦ በበቂ ቅድመ ዝግጅት፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራችን እና በከፍተኛ አመራሮቻችን ልዩ ትኩረት የተመራ ሲሆን የክልላችን ሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት የተካሄደ ታሪካዊ እና ልዩ ቦታ የሚሰጠው መድረክ ነው፡፡

የውይይት መድረካችንን ታሪካዊ እና ልዩ የሚያደርገው ከዛሬ ስምንት ወራት በፊት ክልላችን ገብቶበት ከነበረው የሰላም ቀውስ እና ጽንፈኛ እና የታጠቁ ኀይሎች ክልላችንን አፍርሰው በኀይል ስልጣንን ከሕዝብ ለመንጠቅ ያደረጉትን ከፍተኛ ሙከራ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፤ በክልላችን የፀጥታ ኀይል፣ በአመራራችን እና በሕዝባችን ክቡር መስዋዕትነት ቀልብሰንና ሕዝባችንን አረጋግተን፤ ሰላማችንን አፅንተን፤ ክልላችንን እና ሕዝባችንን ወደ መደበኛ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ከፍተኛ ትግል እያደረግን ባለንበት፤ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዊያን የቅኝ ገዥነትን አመለካከት እና ተግባር ድል በማድረግ ለሁሉም የዓለም ጥቁር እና ጭቁን ሕዝቦች ኩራት የሆነውን የዓድዋ 128ኛ የድል በዓል በድምቀት ባከበርንበት ማግሥት መሆኑ ነው፡፡

ይህ ታሪካዊ እና ልዩ የክልላችንን ወቅታዊ ጉዳዮች በጥልቀት የገመገምንበት የውይይት መድረክ ዓላማ አድርጎ የመከረው ጥልቀት ካለው ዓለማዊ፣ ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ የሁኔታ ግምገማ በመነሳት አሁን የምንገኝበትን ክልላዊ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ በመስራት የተረጋጋ ክልላዊ ሁኔታን መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

የውይይት መድረካችን ዓለማዊ፤ ሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን አካቶ የክልላችን ያለፉት ስምንት ወራት ወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ሁኔታችንን ለማሻሻል እና በዘላቂነት ሕዝባችንን እና ክልላችንን ወደ

ተሟላ ሰላም ለማምጣት በተሠሩ ሕግ የማስከበር ሥራዎች፤ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት እና የድርጅት እና የሕዝብ ግንኙነት ተልዕኮዎች የተገኙ ውጤቶችን በእውነት እና በእውቀት እንዲሁም በጥልቀት ለመገምገም ያስቻለን ሲሆን ቀሪ ተልዕኮዎቻችን ላይም ባካሄድናቸው ግምገማዎች የጋራ

ድምዳሜ እንድንይዝ ያስቻለን ነበር፡፡

የውይይት መድረካችን አሁን የምንገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በሕዝባችን ግፊትና ጥያቄዎች እንዲሁም በፓርቲያችን መሪነት ከተረጋገጠው ሀገራዊ እና ክልላዊ ለውጥ የተገኙ ድሎችን እና ፈተናዎችን በጥልቀት አይቷል፡፡ የአማራ ሕዝብ የለውጥ መድረኩ ባለቤት ነው፡፡ በለውጡ መድረክ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ የሚፈቱለትን መሰረታዊ ጥያቄዎች አንጥሮ ለይቷል፡፡ ጥያቄዎቹም አንዳንዶቹ ምላሽ ማግኘት በጀመሩበት እና ሌሎቹም ከኢትዮጵያዊያን ወንድም እህቶቻችን ጋር በጋራ ሆነን ምላሽ ለማሰጠት የህዝባችንን ቃል አክብረን ትግል ላይ ሳለን ለውጡ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እንዲያልፍ መገደዱም ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያን ኃያልነት እና ጠንካራ ቀጣይነት የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለውጡን ለመቀልበስ ርብርብ ሲያደርጉ፤ የህልውና ጦርነቱ ለከፍተኛ ውድመት ሲዳርገን፤ ተላላኪዎቹ ደግሞ ህዝባችንን ለዘርፈ-

ብዙ ሰቆቃ የዳረጉን መሆኑም እንዲሁ የአደባባይ ሃቅ ሆኖ ሳለ ከውስጣችን የበቀሉ ጽንፈኛ እና ዘራፊ ኃይሎች “የህዝብን ጥያቄ ሽፋን አድርገው”፣ ከውስጥም ከውጭም አጀንዳ ከሚሰጣቸው የጠላት ኀይል ጋር ተሰልፈው፤ በድህረ-እውነታ ፖለቲካ በሚዘወረው የጥፋት ሚዲያ ታግዘው፤ ክልላችን እና ሀገራችን በማፍረስ ህዝቡን ለጉስቁልና ለመዳረግ የጭካኔ በትራቸውን ያሳረፉብን ሲሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነን በከፍተኛ መስዋዕትነት ሀገር የማፍረስ አጀንዳቸውን ሙሉ በሙሉ ቀልብሰናል፡፡

አሁን ደግሞ ሕዝባችንን ለዘመናት ሲያጎሳቁሉ የነበሩ ኃይሎች የውስጣዊ ሁኔታችን የተዳከመ ሲመስላቸው

አንገታቸውን ቀና በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ትንኮሳዎችን ለመፈፀም ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው፡፡ ይሁን እንጅ ህዝባችን እንደተለመደው በችግር ውስጥም ሆኖ ህልውናውን እና አንድነቱን የሚፈታተነውን ዕኩይ ኃይል ሁሉ በተባባረ ክንድ መክቶ አንድነቱን ያስቀጥላል፡፡

የውይይት መድረካችን ያለፉትን 8 ወራት የህልውና ትግሎች በተለያዩ ምዕራፎች ከተፈፀሙ ወሳኝ ተልዕኮዎች አንፃር በጥልቀት የገመገመ ሲሆን የክልሉን አመራር በየደረጃው እንደገና በማደራጀት፤ የፀጥታ ኀይላችን ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በማቀናጀት፤ ከሕዝባችን ጋር በሰፋፊ የሕዝብ ግንኙነት መድረኮች በመግባባት እና ሃይል በማሰባሰብ የጽንፈኛውን ሀገር የማፍረስ የጥፋት ተልዕኮ ቀልብሰን፤

ሕዝባችን በማረጋጋት ወደ ተሟላ ሰላም የማፅናት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ እንገኛለን፡፡

ከሕግ ማስከበር ሥራችን ጎን ለጎንም ባለፉት 8 የፈተና ወራት በቀላሉ የማይታዩ የልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎችንም አከናውነናል፡፡ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ተፈናቃዮችን ወደ

ቀያቸው የመመለስ ስራ ጀምረናል፡፡ ከሰላም እጦቱ በተጨማሪ የገጠመንን የድርቅ ችግር ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ርብርብ አድርገናል፡፡ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልላችን የጀመራቸውን ስራዎች በመደገፍ ስራውን የማሳለጥ ስራ ተጀምሯል፡፡ በዚህም ክልላችን አንፃራዊ ሰላም ወደአለበት ነባራዊ ሁኔታ

እንዲሸጋገር አስችለነዋል፡፡

ውድ የፓርቲያችን አመራሮች፤ አባላት፤ ደጋፊዎቻችንና መላው የክልላችን ሕዝቦች! 

በክልላችን የታየው የጽንፈኝነት አመለካከትና ተግባር ከህዝባችን እሴት እና ታሪክ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ- የብሔረ-ሀገር ግንባታ አበርክቶው በተቃራኒው ህዝባችን አንገት ያስደፋ ቢሆንም ዛሬም አመራራችን በፀጥታ ችግርም ውስጥ ሆኖ ከህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳይዛነፍ ለተፈፃሚነታቸው ክፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ ህዝባችን ለበርካታ አስርት ዓመታት የታገለባቸው የማንነትና ወሰን ጥያቄዎች፤ የህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ድንጋጌዎች፤ ስሁት የሆኑ የፖለቲካዊ ትርክት እርማቶች፤ ፍትሃዊ የሆኑ የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄዎች፤ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበር ላይ የሚታዩ ዝንፈቶችን ለመግራት አሁንም ያላሳለሰ የፖለቲካ ትግል ላይ ነን፡፡ ሆኖም የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረገው ትግል እልህ አስጨራሽ፤ የተራዘመና ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ጽንፈኛ ኃይሉ በክልላችን የደቀነው የጸጥታ ስጋት እና አውዳሚ የትግል አግባብ በጥያቄዎቻችን ምላሽ አሰጣጥ ላይ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ርብርብ እንዳናደርግ እንቅፋት መሆን ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የውጭ ጠላት አቅም እየሆኑ መሆኑን ህዝባችን በውል ልብ ሊለው ይገባል፡፡

ፓርቲያችን ብልጽግናም ከፕሮግራሞቹ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅምና ፖለቲካዊ ምህዳር አለው፡፡ በአጠቃላይ አሁን ለምንገኝበት የፖለቲካ መድረክ ክልላችንን ወደ አስተማማኝ ሠላም የመመለስ እና የህዝባችንን ሰላም መሻት የማፅናት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠው የህልውና ትግል መሆኑን በውይይታችን ተግባብተናል፡፡ ህዝባችን አብዝቶ ሰላም ወዳድ ነው፡፡ ጽንፈኛው ሃይል በህዝባችን ላይ ሰፋፊ ግፍ እና በደል ፈፅሟል፡፡ ህዝባችን ይህን በጽንፈኛው እና ዘራፊው ሃይል የሚፈጸምበትን ግፍና በደል ከዚህ በላይ የሚሸከምበት ትከሻ የለውም፡፡ መንግስት ሰላሙን እንዲያስከብርለት ደጋግሞ እየጠየቀ ነው፤ ለዚህም ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከክልላችን የፀጥታ ሃይሎች ጋር እንዲሁም ከአመራራችን ጋር በመቀናጀት እየሰራ በመሆኑ በበርካታ የክልላችን አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ ይህን ሰላማዊ ሁኔታ በቀሪ ውስን አካባቢዎች ለማረጋገጥ ከህዝባችን ጋር ሁነን መስራት እና አመራር ማረጋገጥ የሚገባን ስለመሆኑ በውይይታችን ተግባብተናል፡፡

የክልላችን መንግስት በሀገራችን ለመገንባት ትግል በሚደረግበት የዴሞክራሲ ስርዓት ልምምድ ውስጥ

የህዝባችንን ይሁንታ አግኝቶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካታች መንግስታዊ ስርዓትን ዕውን ያደረገ

ለውጥ መንግስት ነው፡፡ ጽንፈኛውና ዘራፊው ሃይል ይህን የዴሞክራሲ ልምምድ ወደ ዜሮ ድምር በመለወጥ የመንግስትን ስልጣን በጠብመንጃ ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ እጅግ ኋላ ቀርና ህዝባችንን ለእንግልት የሚዳርግ እና ሀገር አልባ የሚያደርገን ተግባር መሆኑን ህዝባችን ሊያወግዘው እና ሊፋለመው

ይገባል፡፡

እኛ ትግል የምናደርገው ለህዝባችን የገባነውን ቃል ለማክበር እና ለመፈጸም ነው፡፡ የህዝባችንን መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄዎች ለአፍታም ቢሆን በስንፍና ወደ ጎን የምንላቸው ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት

ማዕቀፍ ምላሽ እንዲያገኙ ትግል የምናደርግባቸው ናቸው፡፡ ሁሌም የአማራ ህዝብ ለአፍታም ቢሆን ከኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ የተነጠለ ህልውና ኖሮት አያውቅም፤ ሊኖረውም አይችልም፡፡

በመሆኑም እንደ ክልል በፅንፈኛው ሃይል የተደቀነብንን እና አጋጥሞን የነበረውን የመፍረስ የህልውና አደጋ ቀልብሰን ለህዝባችን የገባናቸውን ቃሎች በሙሉ አቅም ወደ መመለስ እንድንሸጋገር በማሰብ “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል ባካሄድነው የውይይት መድረክ አሁን ለምንገኝበት የሰላም እጦት የዳረጉንን መሰረታዊ መንስኤዎች በመለየት፤ ያስመዘግብናቸውን ውጤቶች በማስፋት እና በማፅናት እንዲሁም ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ክልላችንን እና ህዝባችንን ወደ ተሟላ እና የፀና ሰላም የሚያሻግሩን ተልዕኮዎችና ተግባራት ላይ ተግባብተናል፡፡

በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በውይይት መድረካችን የደረስንባቸውን ማደማደሚያዎች የሚያረጋግጡ የሚከተሉትን ባለ 9 ነጥብ ነጥብ የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው አዘጋጅተናል፡፡

1ኛ. ጽንፈኛው ኃይል በክልላችን ላይ ደቅኖት የነበረውን በኃይል መንግስትን በማፍረስ ህዝባችንን ለማያቋርጥ ጉስቁልናና እንግልት የመዳረግ ብሎም ኢትዮጵያን በቀጣይነት የመበተን አደጋ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እና የክልላችን የፀጥታ ሃይል ክቡር መስዋዕትነት እንዲሁም በህዝባችን አስተዋይነት ቀልብሰነዋል፡፡ ክልላችንን አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት ክልል ማድረግ የተቻለ ሲሆን ውስን አካባቢዎች አሁንም በሰላም እጦት እና ህዝባችንም ለእንግልት እና ዘረፋ ተዳርጎ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የህዝባችንን የሰላም አስከብሩልን ጥያቄ በዋና አቅምነት በመጠቀም እና ህግ የማስከበር

ዘመቻችንን አጠናክረን በማስቀጠል ክልላችንን እና ህዝባችንን ወደ ተሟላ ሠላም ለመመለስ እንደምንሰራ

ቃል እንገባለን!

2ኛ. በሀገራችን እና በክልላችን ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑ መሰረታዊ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ላይ ዛሬም እንደ ትላንቱ የፀና አቋም ይዘን ትግል እያደርግን ሲሆን ፓርቲያችን ብልፅግና እና እሱ የሚመራው መንግስታችንም ጥያቄዎቹን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ ይገኛል፡፡

የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በህግ አግባብ ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግም ሁለንተናዊ ቅቡልነት ያለው የስርዓተ-መንግስት እንዲገነባ እና ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድም እና እህት ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለማፅናት ወሳኝ እንደሆነ ለዚህም ህዝባችን ትግሉ የሚጠይቀውን ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት ከፍሏል፤ እየከፈለም ይገኛል፡፡

በመሆኑም የወሰን እና የማንነት፤ የዜጎች መብት፤ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያዎች፤ የስሁት ፖለቲካዊ ትርክቶች እርማት እና የመሳሰሉትን ውለው ያደሩ የአማራ ሕዝብ

ጥያቄዎችም ሆነ አሁናዊ የአማራ ሕዝብ ፍላጎቶች በፓርቲያችን አንዳንዶቹ እየተፈቱ ቢሆንም ቀሪዎቹን በትግል ለመፍታት እሰራን እንገኛለን፡፡

በመሆኑም እኛ የአማራ ክልል አመራሮች ያሉብንን ችግሮች አርመን፤ ምሁራንን፤ ሲቪክ አደረጃጀቶችን የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችንና መላው ሕዝብችንን አስተሳስረን፤ በጋራ እየመከርን የጋራ መፍትሄዎችን እያስቀደምን፤ ለዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎቻችን ቅደም ተከተል አስቀምጠን ችግሮችን ለመፍታት የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘንድ ሙሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህ አግባብ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶቹን ለማሳካት እንደ አመራር አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ቃል እንገባለን !

3ኛ. እኛ ብልፅናዎች ነን፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና የጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ሳንካዎችን በማረም መላ ኢትዮጵያዊንን ያቀፈ-የፖለቲካ ዐውድን የፈጠረ፤ የፖለቲካዊ የኀይል ሚዛንን

የሚያሰባስብና በሕብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት ማዕቀፍ የተዋጀ፤ በብሔራዊነት ገዥ ትርክት መላ ኢትዮጵያዊያንን አቅፎ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚሰራ የፖለቲካ አደረጃጀት ባለቤቶች ነን፡፡

በመሆኑም በፓርቲ ግንባታ ስራችን መላው አባላችንና ደጋፊዎቻችን በማነቃነቅ፤ በየደረጃው የአመራር ስርዓታችን በጥራት፤ ውጤት፤ ቀጣይነት፤ አካታችነት እና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ የምንሰራ ሲሆን፤ የፓርቲ አደረጃጀቶቻችን በአግባቡ ተደራጅተው ቀጣይነት ባለው ግንኙነትና ግንባታ ሂደት የተጀመረውን ለውጥ በግምባር ቀደምትነት እንዲመሩ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ፤ የፓርቲውን ውስጣዊ ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል ተከታታይነት ያለው አመራር እና አባላት የማጥራት ስራ በመስራት እንዲሁም የአመራር ምዘና በተያዘለት ጊዜ እንዲከናዎን በማድረግ፤ ውይይትና ግምገማ በማካሄድ በየደረጃው ያለውን አመራር እና አባላት ተቀራራቢ የፖለቲካ አመለካከት እንዲይዝ በማድረግ የተጀመረውን የፖለቲካና ድርጅት ስራ በማጠናከር የፓርቲያችንን የመፈጸም እና የማስፈፀም ብቃት እናሳድጋለን !

4ኛ. የክልላችን ጸጥታ ወደ ተሟላና የተረጋጋ ሰላም እንዲመለስ ከምንሰራው የህግ ማስከበር ስራ ጎን ለጎን፤ የሰላም እና ልማት ስራዎቻችን የማይነጣጠሉ እና የሚመጋገቡ መሆናቸውን በውይይት መድረኩ በጥልቀት ገምግመናል፡፡

በመሆኑም የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ስራችን በሁሉም የግብርና ልማት ዘርፎች በችግር ውስጥም ሆኖ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ በተፈጥሮ ሀብት፤ በሰብል ልማት፤ በአትክልትና ፍራፍሬ፤ በእንስሳሳት ሃብት ልማት ስራዎች እና በመሳሰሉት ከፍተኛ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክልሉ ካለው እምቅ የግብርና ልማት አቅም አኳያ ሲታይ ቀሪ ርብርብ የሚጠይቁ ስራዎች እንዳሉ አይተናል፡፡ በተለይም የአርሶ አደሩን የመልማት እና ፍትሃዊ ጥያቄዎቹን ማዕከል በማድረግ የማዳበሪያ፤ ምርጥ ዘር እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረቶቹን መፍታት እንደሚገባም ተግባብተናል፡፡

በክልላችን የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፤ የኑሮ ውድነት፤ የኢንዱስትሪ ልማት፤ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች፤ በትምህርትና የጤና ልማት ስራዎች የተገኙ ውጤቶችና ያሉብንን ጉደለቶች በጥልቀት የገመገምን ሲሆን አጋጥሞን በነበረው የሰላም እጦት በግብርና የልማት ስራ፤ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፤ በኢንዱስትሪ እና በማዕድን ሐብት ልማት ስራ፤ በቱሪዝም ሃብት ስራችን ላይና በማህበራዊ ልማት ሰራዎቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ማሳደሩን ገምገግመናል፡፡ ከዚህ ጋር

ታያይዞም የኑሮ ውድነቱ የበለጠ ማህበረሰቡን እያማረረ ያለ እንደሆነ በጥልቀት አይተናል፡፡

ስለሆነም፤ እኛ የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያቀድናቸውን የልማት ስራዎች በውጤታማነት እና በተደራጀ ንቅናቄ በማሻሻል የክልላችን ህዝብ የልማት ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ እና በልዩ ንቅናቄ ለመስራት ቃል እንገባለን !

5ኛ. የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመፈፀም የክልላችን ዕድገት ለማፋጠንና የህብረተሰባችንን እርካታ ለማረጋገጥ የክልላችን የገቢ አቅም ማሳደግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ

ባሳለፍናቸው ወራት በችግር ውስጥም ሆነን አርሶ አደሩ እና የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር ለመክፈል ያሳየው ቁርጠኝነት እና የተሰበሰበው ገቢም አበረታች ነው፡፡ ነገር ግን ጽንፈኛው ኃይል በክልላችን በፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የገቢ አቅማችንን አሟጠን እንዳንሰበሰብ ከፍተኛ እንቅፋት የፈጠረ መሆኑን ገምግመናል፡፡ ስለሆነም በቀሪ ጊዚያት አሁን ላይ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም የበለጠ በማፅናት እና እግር በመትከል የገቢ አቅማችንን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንሰራለን !

6ኛ. የመልካም አስተዳደር ጉድለት መገለጫ የሆኑ ከአገልግሎት አሰጣጣችን ጋር የተያያዙ ዘርፈ-ብዙ ጉድለቶች እና የፍትህ ስርዓታችን የሚገኝበትን ቁመና ብሎም የህዝብ አመኔታ ጉዳይ በጥልቀት

ገምግመናል፡፡ ሌብነት እና የብልሹ አሰራር ተግባርና አሰተሳሰብ በሕዝባችን እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ላይ እያሳደረ የሚገኘው ጫና ከፍተኛ መሆኑን እና ህዝባችንን ለምሬት የዳረገ ጉዳይ መሆኑንም አይተናል፡፡

በፍትህ ስርዓታችን ላይ የህዝባችን አመኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሳ የመጣ መሆኑን ገምግመናል፡፡ በመሆኑም አገልግሎት አሰጣጥ እና ውሳኔ የመስጠት አቅማችንን ማሳደግ፤ መንግስት የጀመረውን የፍትህ ተቋማት ሪፎርም ስራ በአግባቡ መምራት እንደሚገባን እና ፈፃሚውን አካልም በአገልጋይነት መንፈስ ሪፎርም በማድረግ ለመስራት ተግባብተናል፡፡ በመሆኑም እኛ የዚህ መድረክ ተሳታፊ አመራሮች በክልላችን የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ቆጥሮ በመፍታት እና የፍትህ ተቋማት ሪፎርሙን በትጋት በመፈፀም የህዝባችን እርካታ እናሻሽላለን !

7ኛ. የጽንፈኝነት አስተሳሰብም ሆነ ድርጊት ለማንኛውም ሀገር፤ ሕዝብ፤ ግለሰብ፤ ባህላዊም ሆነ ኃይማኖታዊ እሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አውዳሚ አደጋ ነው፡፡ ይህንን አውዳሚ አስተሳሰብ በወቅቱ የማከም እና የመግራት ተጨባጭ ስራዎች ካልተፈጸሙ የሀገራችንም ሆነ የክልላችንን ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በማመሰቃቀል እንደ ሀገር ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን በጥልቀት ገምግመናል፡፡

በክልላችን በተጨባጭ እየሆነ ያለው ይኸው አሳዛኝ ሁነት ነው፡፡ ሥለሆነም የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶች በሀገር ሉዓላዊነት እና በሕዝብ ሁለንተናዊ ሕልውና ላይ እያሳደረ ያለውን ግልጽ አደጋ ለመቀልበስ በየደረጃው የሚገኘው የፓርቲያችን አመራር የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶችን አደጋ በማጤን፤ ራሱንም ከዚህ አደገኛ አስተሳሰብ ሰለባነት ታድጎ፤ የጽንፈኝነት አስተሳሰብናድርጊትን የማክሰም ተግባር ከአንገብጋቢነቱ ባሻገር ጊዜ የማይሰጥ ተጨባጭ አደጋ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የዚህ የውይይት መድረክ ተሳታፊዎች መላ ሕዝባችንን በማስተባበር የተጀመረውን የጽንፈኝነትን አስተሳሰብ እና ግባር አምርሮ በመታገል ክልላችንን ከጽንፈኝነት አደጋ ለመታደግ ቃል እንገባለን!

8ኛ. ክልላችን ከዚህ በላይ ከተገለፁ ዘርፈ-ብዙ ተልዕኮዎች በተጨማሪ በወቅታዊነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየፈፀማቸው ባሉ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች፤ ለድርቅ አደጋዎች ምላሽ መስጠት፤ በተለያዩ ወቅቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመልስና የማቋቋም እንዲሁም ዘርፈ-ብዙ ጥያቄዎቻችን ምላሽ የሚያገኙበት

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራትን አቀናጅቶ እና በልዩ ትኩረት እየተፈፀሙ መሆኑን ገምግመናል፡፡ ሰለሆነም እነዚህን ወሳኝና ወቅታዊ ተግባራትን አካተን በክፈተኛ ትኩረት ለመፈፀም ቃል እንገባለን!

9ኛ. የሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ስራችን በክልሉ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ስራዎቻችን ውስጥ ለህዝባችን መረጃ በመስጠት እና የልማት ስራዎችን በማሳለጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው

ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት አጠቃላይ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራችን በክልሉ በሚደረገው ህግ የማስከበር ተልዕኮና እና የልማት ስራዎች እንቅስቃሴ ለህዝባችን መረጃ በመስጠት እና ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር መሻሻሎች እያሳየ መሆኑን አይተናል፡፡ ነገር ግን አሁንም የጽንፈኛ ሚኒዲያውን አፍራሽ ቅስቀሳ እና የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ለማምከን የሚችል የተደራጀ እና የተቀናጀ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በመስራት በኩል ሰፊ ጉድለቶች ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም የሚዲያን እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ያላቸውን ሚና

በውል በመረዳት፤ ጠንካራ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝባችን

ጋር መግባባት ለመፍጠር እንሰራለን !

በአጠቃላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ በአራቱም ኮማንድ ፖስት የህግ ማስከበር ስራውን እየገመገሙ በመምራት ክልላችን ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመጣ ላደረገው ተከታታይነት ያለው የአመራር ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋናችን እያቀረብን የተጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሙሉ

እምነታችን ነው፡፡ ለዚህም ስኬት ርብርብ ላደረጉ ለጀግናው መካላከያ ሰራዊታችን እና የጦር መኮንኖች እና አባላት፤ ለመላው የክልላችን የጸጥታ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ ህዝባችን ከልብ

የመነጨ ምስጋና እናቀርባለን።

በመጨረሻም፡- መላው የፓርቲያችን አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎቻችን ላለፉት ቀናት በአማራ ክልል ያጋጠሙ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልበትን መፍትሄ ለማስቀመጥ ባካሄድነው ውይይት የደረስንባቸው ድምዳሜዎች ተግባራዊ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የእናንተን ሙሉ ድጋፍ እና ርብርብ ይጠይቃሉ፡፡ ስለሆነም በክልላችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ያላሰለሰ ጥረታችሁንና ሁለገብ ሚናችሁን እንድትጫወቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን!

እንዲሁም፡- መላው የክልላችን ሕዝብ እና ኢትዮጵያውያን፤ ዲያስፖራዎች፤ ምሁራን እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ክልላችን ከገጠመው አደጋ ለመታደግ በሰራቸው ስራዎች ያገኘናቸው ድሎች እንዳሉ

ሆኖ በአንጻሩ ደግሞ ድክመቶች እንዲታረሙ በማድረግ የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር

ሕዝባችንን ለማሻገር የበኩላችሁን አዎንታዊ ሚና እንድትወጡ ስንል የከበረ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን !

ቃላችንን እናከብራለን! በዘላቂነት እግር እንተክላለን!

የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች!

መጋቢት 5/2016 ዓ.ም

ባሕር ዳር


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top