አዲስ አበባ የላቀች የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አደራ መወጣታችን የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ያስፈልጋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለፁ፡፡
37ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ በሰላምና ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋፆ ላደረጉ አካላት የእውቅናና የምስጋና አሰጣጥ መርሐ ግብር በብሔራዊ ኮሚቴ አማካኝነት ተከናውኗል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ይህንን ሀላፊነት ክብሩን በሚመጥን አኳኋን በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉም አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ መስተንግዶ በስኬት በማዘጋጀት ያዳበርነውን ባሕላችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ በጉባኤው የተሳተፉ ከተለያዩ አገራት የመጡ እንግዶችን የተቀላጠፈ አቀባበል እና አሸኛኘት በማድረግ የተሟላ አገልግሎት ለሰጡ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
በእውቅና መርሃ-ግብሩ አስተዋጽኦ ላደረጉ የተለያዩ ተቋማት ከአምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የምስጋና እና እውቅና የምስክር ወርቀት መበርከቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።