ሕጋዊ ራስን የመከላከል ድርጊት

1 Mon Ago
ሕጋዊ ራስን የመከላከል ድርጊት

አቅም በፈቀደው መጠን ከጉዳት ወይም ከጥቃት ራስን ለመከላከል መሞከር የሰዎችም ሆነ የእንስሳት ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው።

የሚመጣብንን ጥቃት አቅሙ ካለን አጥቂውን አሸንፈን፤ ከሌለንም ሸሽተን ራሳችንን ከሚደርስብን ጉዳት መጠበቅ ቅፅበታዊና ሥነ -ሕይወታዊ ምላሽም ነው፡፡

ይህ ተፈጥሯዊ መብት በሕግ ሊገደብ የማይችል ፍፁማዊ መብት ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ መብት ስንጠቀም በሌላ ሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት ብናደርስ በወንጀል ላያስጠይቀን የሚችልበት አግባብ ‘ሕጋዊ መከላከል’ን ካላለፈ መሆኑ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 78 ላይ ተቀምጧል።

አንድ ድርጊት ሕጋዊ መከላከል ነው የሚባለው የሚከተሉትን ሦስት ሁኔታዎችን አሟልቶ ሲይዝ ነው፡-

ሀ. ጥቃት፡- የራሱን ወይም የሌላ ሰው መብት ላይ ከሚሰነዘር ወይም ሊደርስ ከተቃረበ ሕገወጥ ጥቃት ለማዳን መሆን አለበት፡፡

ለ. አማራጭ ማጣት፡- ጥቃቱ እንደይደርስ ለማድረግ ሌላ መንገድ አለመኖሩ።

ሐ. ተመጣጣኝ ምላሽ፡- ከጥቃቱ ሁኔታ መጠን ባለማለፍ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ በመውሰድ የሚፈፀም መሆን አለበት።

አንድ ሰው በሕጋዊ ራስን መከላከል አግባብ በሌላው ላይ የሚወስደው እርምጃ በወንጀል የማያስጠይቀው ድርጊቱ ከላይ የተቀመጡትን ሁኔታዎች ሲያሟላ ነው፡፡

እስኪ እስከ ፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ ሁለት የሕጋዊ መከላከልን የሚመለከቱ የወንጀል ክርክሮችን እናንሳ፡፡

የቡቼ ግድያ

ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ለቡቼ/ለብስራት ተፈሪ/ የመጨረሻ ቀኑ ሆነች፡፡ ሀዋሳ ፋሚሊ ሆቴል በመጠጣት ላይ የነበረው ቡቼ እና የሆቴሉ ባለቤት አቶ ጌታቸው ገላዬ ይጣላሉ።

በሆቴሉ የነበሩት ሰዎች ገላገሏቸውና ቡቼ ወደ ቤቱ ሄደ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቡቼ መልሶ መጣና ወደ ሆቴሉ ገባ በቀጥታም ወደ አቶ ጌታቸው አመራ፡፡

ይሔኔ ነበር ‘ሳይቀድመኝ ልቅደመው’ ያሉት አቶ ጌታቸው ገና አጠገባቸው ሳይደርስ ሽጉጣቸውን ሲመዙ ሰይፈ የተባለው ሰው ደግሞ የውስኪ ጠርሙስ ጨብጦ ቡቼን ‘እንዳትንቀሳቀስ!’ ያለው።

በዚህ መሐል ነበር አቶ ጌታቸው  ሽጉጣቸውን የተኮሱት። ቡቼም በተኮሱት ጥይት ግራ ብብቱ ላይ ተመታና ሞተ፡፡   

አቶ ጌታቸው ሆን ብለው ቡቼን በመግደል እና ሰይፈ ደግሞ በውስኪ ጠርሙስ አስፈራርቶ ቡቼን በማስቆም እንዲሁም የተመታበትን ቀለህ በመደበቅ በወንጀል ተባባሪነት በሀዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ ቀረበባቸው፡፡

አቶ ጌታቸው ‘‘ቡቼን የገደልኩት 'በሕይወት አትኖራትም' ብሎ ዝቶብኝ ከሄደ በኋላ ሳንጃ ይዞ ተመልሶ በመምጣት ሊገድለኝ ሲል ሌላ አማራጭ ስላልነበረኝ ነውና ድርጊቴ ሕጋዊ መከላከል ነው።’’ ብለው ተከራከሩ።

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ሰምቶ የአቶ ጌታቸው ድርጊት በሕጋዊ መከላከል ስር ስለማይወድቅ በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ። (የሁለተኛውን ተከሳሽ የሰይፈን ጉዳይ፤ በነፃ ይሰናበት ወይም ቅጣቱን ተቀብሎ ይቅር ታሪኩን ያገኘሁበት የሰበር ውሳኔ ስለማይገለፅ አላወኩም።)

 አቶ ጌታቸው ግን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረቡና የቅጣቱ መጠን ወደ 8 ዓመት ተሻሻለላቸው፡፡ ወደ ክልሉ ሰበር ሰሚ ቢሄዱም ውሳኔው ፀና።

ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ‘‘ግድያውን የፈፀምኩት ቡቼ ሕይወቴ ላይ ሊያደርስ የነበረውን የቅርብ ጥቃት ለመከላከል ሌላ አማራጭ ስለሌለኝ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ በመቀጣቴ የስር ፍርድ ቤቶች የሕግ ስህተት ፈፅመዋልና የሕግ ስህተቱ ይታረምልኝ።’’ የሚል  አቤቱታ አቀረቡ።

ሰበር ምን ብሎ የሚወስን ይመስላችኋል!? አቶ ጌታቸው ቡቼን የገደሉት በሕጋዊ መከላከል ነው ወይስ አይደለም?  እስኪ ስለ ሕጋዊ መከላከል ያላችሁን ግንዛቤ ተጠቅማችሁ ገምቱ።

ሰበር በጉዳዪ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት አንድ ሌላ ተመሳሳይ  ጉዳይ እናንሳ።

የፖሊሶቹ ድርጊት

ጥር 5 1999 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ቀንጠንቂቻ ቀበሌ ያለው ታንታለም ፋብሪካ አጠገብ አንድ ሰው ይሞታል።

በዛው ዕለት ሌሊቱን ከ300 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ክላሽ፣ ጦር እና ገጀራ ይዘው ተሰበሰቡና ፋብሪካውን ሰብረው ለመግባት ሞከሩ፤ የፋብሪካውን ሠራተኞችም ከቅጥር ግቢው እንዳይወጡና እንዳይገቡ አገዱ።

ይሄኔ ነገሩ ካቅም በላይ ሲሆን፤ የፌደራል ፖሊስ ባልደረቦች ጥሪ ተላለፈላቸውና ፀጥታ ለማስከበር ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በስፍራው ደረሱ።

የመጡበት የፖሊስ ተሽከርካሪና የተወሰኑ የፖሊስ አባላት ላይ ከተሰበሰበው ሕዝብ መሐል የተወሰኑት ሰዎች ጥቃት ሰነዘሩባቸው፤ በዚህ የተነሳ ግጭት ተፈጠረ።

በወቅቱ በስፍራው ከነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል ሳጅን ሸጋ እና ኮንስታብል ሀብታሙ በዲሳ  ፀጥታውን ለማወክ ተሰብስበዋል ከተባሉት ሰዎች መሐል ሁለቱን በጥይት ተኩሰው ገደሉ ።

ሌላኛው ኮንስታብል ሀብታሙ ደግሞ በቀለ ዲሎ እና ዱከሌ ደረሰን ተኩሶ መግደሉ ሳያንስ ተሰብስቦ በነበረው ሰው ላይ ደግኖ በመተኮስ  አራት ሰዎችን አቆሰለ፡፡ (የሰበር አቤቱታው በፌደራል  ፖሊስ በኩል መቅረቡ ተከሳሾቹ ፌደራል ናቸው ብዬ እንድገምት አርጎኛል ውሳኔው ላይ ግን የተጠቀሰው ፖሊስነታቸው ብቻ ነው።)

በፈፀሙት  የሰው መግደልና የግድያ ሙከራ ወንጀል  ሦስቱ ፖሊሶች ተከሰሱ።

ፖሊሶቹ ጥፋተኛ አይደለንም ብለው ቢከራከሩም፤ ክሱ የቀረበለት የጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች እና የተከሳሾችን መከላከያ መርምሮ፤ ረዳት ሳጅን ሸጋ እና ኮንስታብል ሀብታሙ በዲሳን እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት ፅኑ እስራትእንዲቀጡ ወሰነ።

ሌላኛው ኮንስታብል ሀብታሙን ደግሞ ሁለት ሰው ገድሎ አራት ሰው በማቁሰሉ በ20 ዓመት ፅኑ እስር እንዲቀጣ ወሰነ ፡፡

ፖሊሶቹ ይግባኝ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም ውሳኔው ፀናባቸው።

የፌደራል ፖሊስ ነገረፈጅ ተከሳሾችን ወክሎ ‘‘ፖሊሶቹ እርምጃውን የወሰዱት በወቅቱ በተነሳው ግጭት የታንታለም ፋብሪካው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ነው። በተፈጠረው ግጭትም የተወሰኑ የፖሊስ አባላትና መኪናቸው ላይ ጉዳት ደርሷል። ስለዚህ ድርጊቱ የተፈፀመው በሕጋዊ መከላከል በመሆኑ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ ሦስቱ የፖሊስ አባላት በነፃ ይለቀቁልኝ።’’ ሲል ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረበ።

ሰበር የዓቃቤ ሕግን እና የተከሳሾችን ክርክር ከሕጉ አንፃር መርምሮ ውሳኔ ሰጠ፡፡

በፖሊሶቹ ጉዳይ ላይስ የሰበር ውሳኔ ምን ይመስላችኋል? ግምታችሁን በመልዕክት መስጫው ሳጥን ውስጥ አጋሩን።

ሰበር ምን አለ?

የቡቼን ግድያ በተመለከተ ቅፅ 15 ላይ በታተመው በሰ/መ/ቁ 86570 ሚያዝያ 2005 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ‘'ቡቼን የገደሉት አቶ ጌታቸው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሌላ አማራጭ መጠቀም ይችሉ ነበር።

ሆኖም እነዛን አማራጮች (ለምሳሌ መሸሽ ፣ እጁን ወይም እግሩን መምታት፣ በመሳሪያ ማስጠንቀቅ የመሳሰሉትን) አልተጠቀሙም።

ግድያውን የፈፀሙት ሟቹ ያዘው ከተባለው ሳንጃ ጋር ተመጣጣኝ ባልሆነ መሳሪያ (ሽጉጥ) በመሆኑ ተመጣጣኝ በሆነ ዘዴ ወይም መሳሪያ አልተጠቀሙም።

በመሆኑም በቡቼ ላይ የፈፀሙት ግድያ በሕጋዊ መከላከል ስር የሚወድቅ ባለመሆኑ፤ በተራ የሰው ግድያ 8 ዓመት እንዲቀጡ መወሰኑ የሕግ ስህተት አልተፈፀመበትም።’’ በማለት የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አፅንቶታል፡፡

 የሦስቱ ፖሊሶች ላይ የተሰጠው ውሳኔ ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ቅፅ 10 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

በሰ/መ/ቁ 43501 መጋቢት 15 ቀን 2002 ዓ.ም በተሰጠው ውሳኔ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ‘‘የፖሊሶቹ ድርጊት የታንታለም ፋብሪካው ላይ እና አባሎቻቸው ላይ የተቃጣውን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል የተፈፀመ ቢሆንም ‘የወሰዱት እርምጃ የተሰነዘረውን ጥቃት ለማስወገድ ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው መሆኑንና ተመጣጣኝ መሆኑን አስረድተዋል ወይ?’ የሚለውን ጥያቄ መመልከት ያስፈልጋል። ፖሊሶቹ በስር ፍርድ ቤት ባቀረቡት ማስረጃ እርምጃውን የወሰዱት ሕገ ወጥ ጥቃትን ለማስወገድ መሆኑን ቢያስረዱም እርምጃው ሌላውን አማራጭ ያሟጠጠ እንደሆነ እና  እርምጃው ከጥቃቱ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ግን አላስረዱም" ብሏል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ ድርጊታቸው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 79 ስር ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን በማለፍ የተፈፀመ በመሆኑ፤ የተከሰሱበት ተራ የሰው ግድያ አንቀጽ  ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን ማሳለፍን በሚመለከተው ቀላል የሰው ግድያ አንቀጽ እንዲቀየር አድርጎ፤ 1ኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ሸጋ እና 2ኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ሀብታሙ በዳሴ እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት እስር 3ኛው ተከሳሽ ኮንስታብል ሀብታሙ  2 ሰዎች ገሎ 4 ሰው በማቁሰሉ በ5 ዓመት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

ግምታችሁንና የሰበር ውሳኔዎችን እንዴት አገኛችኋቸው?

ለማንኛውም ራስን መከላከል የሁላችንም ተፈጥሯዊ ፍላጎትና መብት ነው ፡፡ ሆኖም ሕግ በሚፈቅደው መልኩ ብቻ መሆን አለበት።

ሕጋዊ የሚሆነው ደግሞ ከላይ ያነሳናቸው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 78 መስፈርቶችን ሲያሟላ ብቻ ነው።

ሕግ አስከባሪዎችም ብትሆኑ ሕጉን ስታስከብሩ የምትወስዱት እርምጃ ሌላ አማራጭ የሌለውና ተመጣጣኝ መሳሪያ ወይም ዘዴ የሚጠቀም መሆን አለበት። አልያ ሕግ ለማስከበር ሕጉን መጣስ ይሆንና ኃላፊነትን ያስከትላል፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top