የ2023/24 የአውሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

1 Yr Ago 166
የ2023/24 የአውሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

32 ቡድኖች በ8 ምድቦች ተደልድለው የሚወዳደሩበት የአውሮፓ ሊግ የምድብ ጨዋታ ዛሬ ይጀመራል፡፡ በመርሐ-ግብሩ አስራ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

የዘንድሮው አውሮፓ ሊግ በታሪኩ ለ53ኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን፣ ስያሜው ከአውሮፓ ዋንጫ ወደ አውሮፓ ሊግ ከተቀየረ ወዲህ 15ኛው መርሐ-ግብሩ ነው፡፡

በምድብ ሁለት ብራይተን ኤኬ አቴንስን ያስተናግዳል፤ ይህ የብራይተን ተሳትፎ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያው የአውሮፓ ጨዋታ ነው። ብራይተን ባለፈው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፤ ይህም በፕሪምየር ሊጉ እስከ ዛሬ ያገኙት ከፍተኛ ደረጃ ሲሆን፣ በዚህም ነው በአውሮፓ ሊግ ለመጫወት የበቃው፡፡

በእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ 5ኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጭ የሆነው ሊቨርፑል ወደ አውስትሪያ በመጓዝ ሊንዘር አትሌቲክስ ስፖርት ክለብ (LASK) ይገጥማል፡፡ 

ቀያዮቹ በክሎፕ መሪነት ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ ኤፍኤ ካፕ እና ካራባኦ ዋንጫን ያሸነፉ ሲሆን፣ በ2015/16 የአውሮፓ ሊግ ፍጻሜ ደርሰው በሲቪያ መሸነፋቸው ይታወሳል።

የክለቡ አሰልጠኝ ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ስለጨዋታው ሲናገሩ “በቡድኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ አዲስ ዋንጫ ለመጨመር እንጫወታለን” ብለዋል፡፡

ቀያዮቹ ውድድሩን የማሸነፍ ግምት ካገኙት ክለቦች መካከል ሲሆኑ፣ አምበሉ ቨርጂል ቫንዳይክ ግን ብዙ ጠንካራ ክለቦች ስላሉ በቀላሉ ሻምፒዮን መሆን እንደሚከብድ ገልጿል።

ባለፈው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜውን ጨዋታ ፊዮረንቲናን በማሸነፍ የኢሮፓ ሻምፒዮን የሆነው ዌስሃም ዩናይትድ ሌላው የእንግሊዝ ተሳታፊ ነው። መዶሻዎቹ ከሰርቢያው TSC ጋር በለንደን ስታዲየም ይጫወታሉ።

የ2023/24 የአውሮፓ ሊግ የውድድር ፍጻሜ 50 ሺህ ተመልካቾቸን በሚይዘው በአየርላንድ ሪፐብሊክ በደብሊን አሬና ይደረጋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top