በአማራ ክልል ፅንፈኛውና ዘሪፊው ቡድን ደቅኖት የነበረው አደጋ በክልሉ ህዝብና በፀጥታ ኃይሎች ትብብር ሙሉ ለሙሉ ተቀልብሷል:- የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አመራሮች

1 Yr Ago 1656
በአማራ ክልል ፅንፈኛውና ዘሪፊው ቡድን ደቅኖት የነበረው አደጋ በክልሉ ህዝብና በፀጥታ ኃይሎች ትብብር ሙሉ ለሙሉ ተቀልብሷል:- የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አመራሮች

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አሥራ ሦስት ቀናት ያከናወናቸውን የተልዕኮ ተግባራት በጥልቅ በመገምገም ቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በሚመለከት አቅጣጫ አስቀምጧል።

የክልሉ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ፅንፈኛውና ዘሪፊው ቡድን ደቅኖት የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ከፍተኛ ሚና ማብርከታቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አመራሮች ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የምእራብ፣ ምስራቅ ማዕከላዊ ሸዋና የጎንደር ቀጠና ኮማንድ ፖስት አመራሮች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም፤ በአማራ ከልል ጽንፈኛውና ዘራፊው ቡድን የመንግሥትን ሥልጣን በሃይል ለመያዝ በማለም በተለይም ታችኛውን የመንግሥት መዋቅር ለመቆጣጠር በስፋት መንቀሳቀሱን ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የአገር መከታ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት በማጥቃት የክልሉን ሰላም ከማወክ ባሻገር፤ አገሪቱን ለውጭ ጠላት የማጋለጥ እኩይ ተግባር ውስጥ መግባቱንም ነው የተናገሩት።

ጎን ለጎንም ቡድኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት ዝርፊያ ውስጥ መግባቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ቡድኑ የክልሉን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ ከማድረግ ባሻገር በርካታ ቁሳዊና ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።  

ጥያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መልኩ ብቻ ማቅረብ እንዳለበት የገለጹት አመራሮቹ፤ ካዛ ውጪ በሃይልና በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ ለየትኛውም አይነት ጥያቄ መፍትሄ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት፤ ፅንፈኛውና ዘሪፊው ቡድን ደቅኖት የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ከፍተኛ ሚና ማብርከታቸውንም ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የአማራ ክልል የኮማንድ ፖስት ቀጠናዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው መመለሳቸውንና ሰላማዊ የሕዝብ እንቅስቃሴም መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡  

በክልሉ ሁሉም ቀጣናዎች የመንግሥት ተቋማት፣ ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ትራንስፖርት፣ የንግድ ተቋማትና ሌሌች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸውን መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አመራሮች፤ በክልሉ ሰላም እንዲመለስ በማድረግ የክልሉ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።      

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top