በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የተሻለ ውጤት እያሳዩ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

1 Yr Ago 257
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የተሻለ ውጤት እያሳዩ ነው - ርዕሰ መስተዳድር  አሻድሊ ሀሰን

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በአሶሳ ዞን አቡራሞ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በአርሶ አደሩ የተከናወኑ የግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የእንስሳት እርባታ እንዲሁም የመኸር ኩታ ገጠም የሰብል ልማት እና የስንዴ ማሳ ዝግጅት ስራዎችን የጎበኙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የግብርና ልማት ስራዎችን በማጠናከር የአርሶ  አደሩን ተጠቃሚነት ለማሻሻል እና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በየደረጃው በሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል የተከናወኑት የግብርና ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው በመሆኑ ስራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መረባረብ ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የሜካናይዜሽን ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል አርሶ አደሩ ውጤታማ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም አቶ አሻድሊ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ በበኩላቸው አርሶ አደሩ በእንስሳት እርባታ እና በሰብል ልማት ውጤታማ እንዲሆን እና ለሸማቹ ማህበረሰብ በቂ የምግብ ግብዓቶችን በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ቢሮው በየመዋቅሩ  ከአርሶ አደሩ ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮችም የጀመሯቸውን የግብርና ስራዎች በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

የአቡራሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጃ በወረዳው እስካሁን ከ61 ሺህ 500 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ አዝርዕቶች የተሸፈነ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ ውስጥ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በበቆሎ ክላስተር የለማ ነው ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመሩት የመስክ ምልከታ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

በጀማል አህመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top