በጥልቅ ግጥሞቿ እና ዜማዎቿ ተውበው በተስረቅራቂ ድምጿ የሚንቆረቆሩት ዘፈኖቿ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ቀለምን የተላበሱ ናቸው።
የተከሰተችው ሙዚቃን በሙሉ ባንድ መሥራት እየቀረ በአንዲት ክፍል ውስጥ ማቀናበር በተጀመረበት 1980ዎቹ መገበዳደጃ ላይ ነበር።
ልዩ ኢትዮጵያዊ ጣዕም ይዛ ብቅ በማለትም "ፀሐይ" የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሟን በገጸ በረከትነት አቀረበች።
በወቅቱ "ፀሐይን" ለማሳተም ከባድ ፈተና ገጠማት። ከዚያ ቀደም የማትታወቅ በመሆኗ እና የራሷን ቀለም ይዛ በመምጣቷ ሙዚቃዋ አይሸጥም ብለው የፈሩት አሳታሚዎች አናሳትምልሽም አሏት።
ሙዚቃ ነፍሷ ስለሆነች ግን በጭራሽ ለፈተናው እጇን መስጠት አልፈለገችም። እናም "ፀሐይ"ን አሳትማ አሰራጨች። የልፋቷን ያህል ግን አልተደመጠላትም።
ምንም ያክል ፈተናው ቢከብዳት፣ እጅ ባለመስጠቷ ውጣ ውረዱን አልፋ የብዙዎችን ልብ አሸንፋ መድመቋን ቀጠለች።
ሁሉም ካለፈ በኋላ ስለገጠሟት ፈተናዎች በጥር ወር 1994 ዓ.ም ለታተመችው ‘ኢትዮጵ’ መጽሔት ስትናገር፣ "ምን ያልገጠመኝ ነገር አለ!፤ ያልረገጥኩት የሙዚቃ ደጃፍ የለም፤ ኦኦ ይቅር ይቅር፤ ሁሉንም ነገር ልዝለለው፤” ብላ ነበር።
አልበሙን (ፀሐይን) ለመሥራት ከአንድ ዓመት በላይ ወስዷል፤ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊቱንም ጭምር እንቅልፍ አልነበረም፤ ትዕግሥት፣ ዕውቀት፣ ችሎታ እና ጉልበት ይህን ሁሉ በገፍ የጠየቀ ሥራ ነው" በማለት ነበር የመጀመሪያ አልበሟን ለማሳተም የነበረባትን ውጣ ውረድ የገለጸችው።
የዛሬው የዐውደ ሰብ ባለተራችን እጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) የተወለደችው በአዊ ዞን፣ ቻግኒ፣ ሰጋዲ ሚካኤል በሚባል አካባቢ ነው።
ቤተሰቧ ጥበብ አፍቃሪ ስለነበረ ገና በልጅነቷ በእናቷ አሠልጣኝነት ከእህቶቿ እና ከጎረቤት ልጆች ጋር በመሆን ቴአትር እየሠሩ ያቀርቡ እንደነበር ራሷ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጻለች።
በ16 ዓመቷም አዲስ አበባ በመምጣት ‘ሴንት ሜሪ’ ትምህርት ቤት ትምህርቷን ጀመረች። ሙዚቃ ልቧን በመውሰዷም ትምህርቷን ችላ አለች፤ በኋላም ከነጭራሹ የቀን ትምህርቷን አቋርጣ ማታ ማታ መማር ጀመረች። የማታ ትምህርቷንም ብዙም ሳትገፋበት አቋረጠች።
በኋላም ለማንም ሳትናገር ወደ ኬንያ በመሰደድ ከስደት አስቸጋሪ ሕወት ጋር መጋፈጥ ጀመረች። እዚያም ከአስቸጋሪው ሕይወት ጋር እየታገለች “ባቲ” የተሰኘ የሙዚቃ ባንድ እስከ ማቋቋም ደረሰች።
ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር ያቋቋመችው "ባቲ" የሙዚቃ ባንድ በኩል የሚያቀርቡት ተወዳጅ እየሆነላቸው መጣ። ቦውሊንግ ግሪን ሆቴል ውስጥ ሲሠሩ በርካቶች ሙዚቃቸውን እየወደዱላቸው መጡ። እዚህም ገና መነሣት ስትጀምር ሌላ ፈተና ገጠማት። እሷም እንደምትለው ሰዎች ባንዱን ባልተገባ መንገድ ለፖለቲካ ሊጠቀሙበት ፈለጉ፤ የሷ ዓላማ ደግሞ ሙዚቃ ብቻ ስለነበረ ተፅዕኖው ሲበዛባት ባንዱን ዘግታ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች።
በዚያ በኬንያ ቆይታዋ ትምህርትም ጀምራ የነበረ ቢሆንም የሙዚቃ ጉዳይ ፋታ ስላልሰጣት በድጋሚ ትምህርቷን አቋረጠች። ሙዚቃ ቀናተኛ ሆናባት፤ ከሷ ውጭ ሌላ ነገር እንዳታስብ እና እንድትሠራ ፋታ አሳጣቻት።
"ፀሐይ" አልበም የታተመው ከኬንያ መልስ ነው። አልበሙን እንዳሳተመች ሳይከፋፈል ወደ አሜሪካ ተጓዘች። ማንነቷን እና ጥበባዊ እይታዋን የገለጡ አልበሞችን የሠራቻቸው በአሜሪካ ቆይታዋ ነበር። ከነዚህ አልበሞች መካከልም “አንድ ኢትዮጵያ”፣ “ጉራማይሌ”፣ “አቢሲኒያን ኢንፋናይት”፣ “ሰም እና ወርቅ” የተሰኙት ይገኙባቸዋል።
ጂጂ ታሪክን እና ባህልን በበሳል ግጥሞቿ፣ በውብ ዜማዎቿ እና በማራኪ ድምጿ መልሳ ስታመጣ ውስጥን ትፈትሻለች። ያላየናትን ትላንት ወደ ቆምንባት ዛሬ አምጥታ ወደ ነገ ተስፋ ታንደረድረናለች። ቁጭትን ውስጣችን ጭራ መንገብገብ ስንጀምር መልሳ ተስፋን ትሰጠናችል። የአባቶቻችን የነጻነት ተጋድሎ ሜዳ ላይ ወስዳ አብራ ታዋጋናለች፤ መልሳ ደግሞ የቆምንበትን እንዳንረሳ ታሳስበናለች።
‘ዓድዋ’ በሚለው ዘፈኗ ላይ ዳሰሳ ያደረገው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ‘የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ሰርክ ገዝፎ የሚንጥ፣ እሩቅ ግን ቅርብ ውብ ስሜት…. ዓድዋ!!’ በሚል ርዕስ ባቀረበው ጹሐፍ፣ ከያኒ ‘አይለወጥም፣ አይነካም ቅዱስ ታሪክ ነው’ ብለን ከታሰርንበት፣ ሀቅ ብለን ካመለክነው አምልኮ አላቅቆ ሌላ መንገድ፣ ሌላ ስርየት እንደሚያጎናጽፈን ሁሉ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዓድዋም ነገረ-መሰረቱ፣ ሌላ እውነት! ሌላ አድማስ! ገዝፎ የሚንጥ፤ እሩቅ ግን ደግሞ ቅርብ ውብ ስሜት አድርጋ አሳይታናለች” ይለናል።
የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዓድዋ፣ ስር እና መንፈሱ ድሮ ጥንት ተጉዞ፤ የሰው ልጅ ‘ሀ’ ብሎ ሲፈጠር ከተሰጠው ጸጋ እና ክብር እንደሚጀመር የሚጠቅሰው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ “የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…” የሚለውን ስንኟን እንደ ዋቢ ያቀርባል። ጂጂ ዓድዋን፣ “የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር” ብላ አሐዱ ያለችበት መንገድ ‘ታሪከ-ዓድዋ’ን ያየችበት፣ ሐቁን የተገነዘበችበት እና እንዲተኮር የፈለገችው ትርጓሜ ነውም ይለናል።
በጠቅላላ ሰባት አልበሞችን ለሕዝብ አድርሳለች። በእነዚህ ሥራዎቿ ተወዳጅ እየሆነች ስትመጣም እንደ ሲኤን ኤን ባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ እንደነ ‘አፍሮ ፖፕ ወርልድ’ እና ‘ሪትም’ የመሰሉ መጽሔቶች አድማቂ ሆነች።
ጂጂ በእነዚህ ሚዲያዎች እንድትቀርብ ያደረጋት የሙዚቃ ስልቷ ነው። ሙዚቃዎቿ በዜማዎቻቸው ለነፍስ ቅርብ የሆኑ፣ በግጥሞቻቸው ውብ በመሆናቸው፣ በቅንብሮቻቸው እና በቪዲዮ ጥራታቸው የላቀ ደረጃ ስላላቸው ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ወገኖች ዘንድም ተወዳጅ ሆነዋል።
ግጥሞቿ ግጥሞች ሀገርን፣ ናፍቆትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ታሪክን ሲገልጹ፤ ለዚህ መነሻዋ ደግሞ ዕድገቷ ነው፤ የኖረችበትን ባህል እና ትውፊት፣ ያየችውን፣ የኖረችውን ከትባ መያዟ ነው።
ጂጂ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላበረከተችው ደማቅ አስተዋፅኦ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት አግኝታለች።
በለሚ ታደሰ