ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፀደቀ

1 Yr Ago 1336
ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፀደቀ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡ 

የሚንስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን፣ 2ዐ15 ዓ/ም ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ በአዋጅ ቁጥር 6/2ዐ15 የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አቅርበዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ የአዋጁን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፤ በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት መፈጸሙንና የተፈጠረውን አለመረጋጋት በመደበኛው የህግ ሥነ ሥርዓት ለማስከበርና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ ይህም የክልሉን መንግስታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ እና የህዝቦችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ማብራሪያውን ተከትሎ በቀረበው ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ዙሪያም በፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ሠፊ ምላሽና ማብራሪያ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ፤ የህዝብን ሠላም፣ የሃገርን ደህንነት እና ህግና ሥርዓትን ለማስከበር በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአዋጅ ቁጥር 1299/2015  በ12 ድምፀ ተአቅቦ በ16 ታቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top