የቡድን 7 አባል ሀገራት ለደሃ ሀገራት 13 ትሪሊዮን ዶላር የልማትና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ድጋፍ መስጠት ይገባቸዋል - ኦክስፋም

11 Mons Ago
የቡድን 7 አባል ሀገራት ለደሃ ሀገራት 13 ትሪሊዮን ዶላር የልማትና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ድጋፍ መስጠት ይገባቸዋል - ኦክስፋም

ባለፀጋዎቹ የቡድን 7 (G7) አባል ሀገራት ለደሃ ሀገራት 13 ትሪሊዮን ዶላር የልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ድጋፍ መስጠት እንደሚገባቸው ኦክስፋም አሳሰበ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ባለፀጋ ሀገራት እና ባንኮቻቸው በተለያዩ ጊዜያት የገቧቸውን ቃሎች በማክበር እና ይህን ግዴታቸውን በመወጣት ፈንታ፤ በየዕለቱ 232 ሚሊዮን ዶላር የብድር ዕዳ እንዲመልሱላቸው ደሃ ሀገራትን በማስጨነቅ ላይ ናቸው ብሏል ድርጅቱ።

"ሀገራቱ ዓለምን የሚታደጓት አዳኞች መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ በተጨባጭ እያነገሱት ያለው ግን ኢፍትሃዊነት እና መድልዎን ነው" ብሏል ኦክስፋም በመግለጫው።

የበለፀጉት ሀገራት እኤአ ከ2020 እስከ 2025 በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ሀገራት ለመስጠት እኤአ በ2009 ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ይህን ሳያደርጉ ቀርተዋል ብሏል ኦክስፋም።

የቡድን 7 አባል ሀገራት ከሰሞኑ በጃፓን ሒሮሺማ በሚደርጉት ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመቋቋም አኳያ ገብተውት የነበረውን ቃል ኪዳን ሊያድሱ ይገባል ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው።

በቡድን 7 አባል ሀገራት ብቻ 6.5 ትሪሊዮን ዶላር ድምር ሀብት ያላቸው 1,123 ቢሊዬነሮች መኖራቸውን የኦክስፋም መግለጫ ይጠቅሳል።

የሀገራቱ የበካይ ጋዝ ልቀት ታዳጊ ሀገራትን ለ8.7 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደዳረጋቸውም መግለጫው ያትታል።

"እናም ሀገራቱ ዕዳቸውን መክፈል ይገባቸዋል፤ ይህን ማድረግ ደግሞ እርዳታ ወይም ውለታ ሳይሆን የሞራል ግዴታ ነው" ብሏል ኦክስፋም በመግለጫው።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top