በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሰብአዊ መብት መከበር ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።

11 Mons Ago
በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሰብአዊ መብት መከበር ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
 
ሪፖርቱን ያቀረቡት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳኒኤል በቀለ፣ አሁንም ትኩረት የሚሹ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እያጋጠሙ ነው ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደብ በመኖሩም ዜጎች እንደፈለጉ ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩ እንቅፋት እየሆነባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 494 ዜጎች ከ1 ሺህ 680 በላይ የሰብአዊ መብት አቤቱታ ማቅረባቸውም ተጠቅሷል።
በ48 ማረሚያ ቤቶች እና 323 ፖሊስ ጣቢያ ላይ ክትትል መደረጉን የገለጸው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ አሁን ላይ በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዙ ከፍተኛ ለውጥ እንዳሳየም በሪፖርቱ አመላክቷል።
በአንፃሩ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር እንዳለ መቀጠሉ ተገልጿል።
አሁንም መንግሥት ሕግ በሚያስከብርባቸው አካባቢዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳያጋጥም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
በሌላ በኩል የሰብአዊ መብት ትምህርት በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ወስጥ እንዲካተት ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሠራቱ በበጎነት ተነሥቷል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ አሁንም ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚያጋጥማቸው ዜጎች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከለውጥ በኋላ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተጠያቂነትን ለማስፈን በነፃነት እና በድፍረት እየሠራ መሆኑ መልካም እንደሆነም አንሥተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው፣ ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር ተያይዞ ያለአግባብ የሚታሰሩ ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚያየው ገልጸዋል።
በቀጣይ መንግሥት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለሰብአዊ መብት መከበር እንዲሠሩም አሳስበዋል።
በአቤል ሙሉጌታ

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top