የ35 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ተፎካካሪዎቹን ክሊያን ምባፔ እና ካሪም ቤንዜማን በማስከተል የዓመቱ የፊፋ የወንዶች ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ማግኘት ችሏል።
በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት በመምራት ዋንጫ ያሸነፈው ሊዮነል ሜሲ በፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ለሁለተኛ ጊዜ ማግኘት ችሏል።
ሊዮኔል ሜሲ በ2021-22 የውድድር ዓመት ለሀገሩ እና ለክለቡ ባደረጋቸው 49 ጨዋታዎች 27 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
‘’በዕድሜዬ እጅግ አስገራሚውን ዓመት አሳልፌለሁ፤ ጥቂቶች ብቻ ማሳካት የሚችሉትን የረዥም ጊዜ ህልሜን ማሳካት ችያለሁ፤ እድለኛም ነኝ፤ ያለ ቡድን አጋሮቼ ይህንን ማድረግ አልችልም ነበር’’ በማለት በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ስሜቱን ገልጿል።
ሽልማቱን በሴቶች የባርሴሎና አሌክስ ፑቴላስ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግርኳስ ተጨዋች በመሆን ማሸነፍ ችላለች።
በምርጥ አሰልጣኝነት የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የአርጀንቲናው አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ ተቀናቃኞቻቸውን ፔፔ ጋርዲዮላን እና ካርሎ አንቾሎቲን በመርታት የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ተብለዋል።
በሴቶች የእንግሊዟ አሰልጣኝ ዊገማን ምርጥ አሰልጣኝ በመባል ተመርጠዋል።
የአርጀንቲና እና የአስቶቪላ ግብ ጠባቂ ኢምሊያኖ ማርቲኔዝ በወንዶች እንዲሁም የእንግሊዟ ሴት ግብ ጠባቂ መሪ ኢርፕስ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች በመባል ተሸልመዋል።
የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ስብስብ ይፋ የተደረገ ሲሆን ቲቦ ኩርቶዋ፣ ሀኪሚ፣ ቫን ዳይክ፣ ካንሴሎ፣ ዲብሮይን፣ ካዝሜሮ፣ ሞድሪች፣ ሜሲ፣ ቤንዜማ፣ ሃላንድ እና ምባፔ ናቸው።