የፌዴራል መንግስት በስምምነቱ መሰረት ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ከህወሓት መረከብ ጀምሯል፡፡
በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬኒያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያ ርክክብ ተደርጓል።
ርክክቡ ከመቐለ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጉላ ካምፕ የተከናወነ ሲሆን፤ በርክክቡ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ታዛቢዎችም ተገኝተዋል።
በቀጠናው የተሰማራው ሠራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በመንግሠታችንና በህወሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሳሪያዎችን መረከባቸውን ገልፀዋል።
ህወሓት ለመከላከያ ሠራዊታችን ያስረከባቸው የመሳሪያ ዓይነቶችም ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርታሮች እና ፐምፐን ያጠቃለለ መሆኑን ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ ተናግረዋል።
የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን ለመታዘብ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች የተገኙ ሲሆን፤ ከአረካካቢዎች መካከል ብርጋዴር ጄነራል አድዋ ልቡካን ፒተር በሁለቱም ወገኖች በኩል እየተደረገ ያለው የከባድ መሳሪያ ርክክብ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰላምን የማስፈን ተግባር ዓለምን የሚስደንቅ መሆኑን ጠቅሰው ለመላው ህዝብና ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።