በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው የሕግ ማስከበር ተግባር አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑ ተገልፀ

3 Days Ago 170
በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው የሕግ ማስከበር ተግባር አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑ ተገልፀ
የአማራ ክልል የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው እና የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
 
የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው፤ በአማራ ክልል የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልፀዋል።
 
ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባለፉት ወራት የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የመሯቸው በርካታ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል ብለዋል። መድረኮቹን ተከትሎም የኃይል አማራጭን ለሚከተሉ ኃይሎች የሰላም ጥሪዎች መተላለፋቸውን አንስተዋል።
 
ለድርድርና ለውይይት መንግስት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም ሊሳካ አለመቻሉንም ተናግረዋል።
በመንግስት የቀረቡትን በርካታ የሰላም እድሎችን በመግፋት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማመቻቸት ጥረት ባደረጉ አካላት ላይ በታጣቂ ኃይሉ አስከፊ ግፎች ተፈፅመዋልም ብለዋል።
 
ይህም ህብረተሰቡን ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ዳርጓል ብለዋል። ታጣቂ ኃይሉ ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ፣ ምርት እንዳይዘዋወር እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
 
የህዝብና የሀገር ሀብትን ከመዝረፍ ባሻገር እገታ በመፈፀም ህብረተሰቡን ከፍተኛ ጉዳት ላይ ጥሎታል ሲሉም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና ድልድዮች ተሰብረዋል ያሉት ሀላፊው፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ተማሪ ቤቱ እንዲውል ከማድረጉም ባሻገር መምህራን ላይ ግድያ ተፈፅሟል ነው ያሉት።
 
ታጣቂ ኃይሉ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም መዳፈሩንም ገልፀዋል።
 
ለሰላም የተዘረጋን እጅ ያልተቀበለ ኃይል ላይ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
 
በሰው እገታ ፣ ግድያ እና መሰል ሕገወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ፣ በመንግስትና በተለያዩ መዋቅሮች የሚገኙ አካላትንም ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረግው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
 
አሁን ላይ በተጨባጭ መረጃ ለይ ተመስርቶ የተለያዩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ የሕግ ማስከበር ስራው እንዲሳካ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
 
የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ የኃይል አማራጭን በመከተል ጫካን የመረጠው ኃይል በክልሉ ሰላማዊ የዜጎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሲያውክ መቆየቱን ተናግረዋል።
 
ይህ ኃይል ዜጎችን በመግደል፣ በማገትና የተለያዩ ግፎችን በመፈፀም ህብረተሰቡን እያሰቃየ መሆኑንም አንስተዋል።
 
ይህንን ሥርዓት ለማስያዝ የመከላከያ ሠራዊቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ የሕግ ማስከበር ስራ እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
 
የክልሉ መስተዳድር እና የፀጥታ ኃይል በተሟላ ቁመና እስከሚደራጅ የሕግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top