በወላይታ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተበት አካባቢ ነዋሪዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉ ተገለጸ

5 Mons Ago 661
በወላይታ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተበት አካባቢ ነዋሪዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉ ተገለጸ
በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከተከሰተበት ቀበሌ ነዋሪዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ የማስፈር ስራ መከናወኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
 
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ እንዳመለከቱት፤ ትናንት በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።
 
በቀበሌው ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ 57 አባወራዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ የማስፈር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
 
በአደጋው ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች የማስጠለል ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ከዚህ ቀደም በዞኑ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ስራ በተቀናጀ መንገድ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው፤ ሆኖም በካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ የተከሰተው አደጋ ተገማች እንዳልነበረ ተናግረዋል።
 
በተጨማሪም በዞኑ በሌሎች ወረዳዎችም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም የጥንቃቄ መልዕክት የማስተላለፍና ነዋሪዎችን የማንቃት ተግባር እተከናወነ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top