ኢትዮጵያ እና ግሪክ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማሙ

1 Mon Ago 216
ኢትዮጵያ እና ግሪክ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማሙ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከግሪክ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር አሌክሳንድራ ፓፓዶፖሉ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በአቴንስ ተወያይተዋል።

በወቅቱም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መንግስት ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎችን በተለይም የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ ብሔራዊ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ እንዲሁም ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አተገባበር አስመልክቶ ለምክትል ሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስኮች የበለጠ ማሳደግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ለዚህም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም በአፅንኦት አንስተዋል። 

የዓለም አቀፍ ተግዳሮት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከቃል የዘለለ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንዳለበት የጠቀሱት አምባሳደር ምስጋኑ፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ላለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ ባደረገችው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች ከ32 ቢሊዮን ችግኞች በላይ መትከል መቻሏን እና በ2025 ወደ 50 ቢሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ምክትል ሚኒስትሯ አምባሳደር አሌክሳንድራ ፓፓዶፖሉ በበኩላቸው፤ በግሪክ እና ኢትዮጵያ መካከል ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን ግንኙነታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተጨባጭ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ትብብሮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ሀገራቸው በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ያላትን ተሞክሮ አንስተው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት ገልጸዋል።

አክለውም ሀገራቱ በንግድ፣ በኢንቨሰትመንት፣ በትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለከታል።

ሁለቱ ወገኖች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር፣ ትኩረት በሚሹ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት እንዲሁም በባለብዙ ወገን መድረኮች ትብብራቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል ከስምምነት መድረሳቸውም ተገልጿል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top