የናኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት እና የአፍሪካ አድናቂዎቹ የ"ጎብኘን" ተማጽኖ

1 Mon Ago 347
የናኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት እና የአፍሪካ አድናቂዎቹ የ"ጎብኘን" ተማጽኖ

የሉዊስ ናኒ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አድናቂዎቹ የ"ጎብኘን" ተማጽኖ እንዲያቀርቡ ማድረጉን ቱኮ የተሰኘው የኬኒያ የድረ-ገጽ ጋዜጣ አስነብቧል። 

ጋዜጣው፥ ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ ዳ ኩና (ሉዊስ ናኒ) ወደ ‘ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ’ ካቀና በኋላ፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አድናቂዎቹ የ"ጎብኘን" ጥሪ እያቀረቡለት ነው ብሏል። 

ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገው ጉዞ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዘንድ ሰፊ የ"ጎብኘን" ጥያቄ እንዲጎርፍለት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል።

 

ለቀድሞው ተጫዋች የ"ጎብኘን" ጥያቄ ካቀረቡ የአፍሪካ ሀገራት አድናቂዎቹ መካከል የጋና፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ናይጄሪያ እግር ኳስ አፍቃሪዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል። 

80ኛ ዓመት የመቻል ስፖርት ክለብ ምሥረታን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ያለው ሉዊስ ናኒ፥ የቤተሰቦቹ መነሻ አፍሪካዊቷ ኬፕ ቬርድ ስትሆን፤ እሱ ግን የተወለደው በፖርቹጋሏ መዲና ሊዝበን ነው። 

እ.አ.አ በ2003 የፖርቹጋሉን ስፖርቲንግ ሊዝበን የወጣቶች ቡድን በመቀላቀል የክለብ ተሳትፎውን የጀመረው ናኒ፥ በ2005 ዋናውን ቡድን በመቀላቀል ከክለቡ ጋር የፖርቹጋል ዋንጫን ሊያነሳ ችሏል። 

ሉዊስ ናኒ ለሀገሩ ፖርቹጋል 112 ጨዋታዎችን በማድረግ 24 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። 

ናኒ በስፖርቲንግ ሊዝበን እያደረገው የነበረው ምርጥ እንቅስቃሴ የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ መልማዮችን ትኩረት በመሳቡ በ2007 ክለቡን ተቀላቅሏል። 

እስከ 2015 በማንችስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ጊዜያት 4 የፕሪሚየር ሊግ፣ 2 የሊግ (አሁን ካራባው ካፕ)፣ 3 የኮሚኒቲ ሺልድ፣ 1 የዓለም ክለቦች እና 1 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል።

 

ከማንችስተር ዩናይትድ ከለቀቀ በኋላ በተለያዩ የፖርቹጋል ክለቦች እና በቱርኩ ፌነርባቼ የተጫወተ ሲሆን፤ ከነዚህ ክለቦች ጋርም የተለያዩ የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ውጤታማ ተጫዋች ነው። 

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top