የሰላም ሠራዊት በጎ ፈቃደኞች - የመዲናዋ ሌቦች ራስ ምታት

1 Mon Ago 269
የሰላም ሠራዊት በጎ ፈቃደኞች - የመዲናዋ ሌቦች ራስ ምታት

የአዲስ አበባ ከተማን ሠላም እና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ፖሊስ ከሠላም ሠራዊት በጎ ፈቃደኞች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል። 

በዚህም በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የስርቆት እና የንጥቂያ ወንጀሎች እየቀነሱ መጥተዋል። 

ከዚህ ቀደም የስርቆት ወንጀል ሰለባ የነበሩት የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አለሙ ሙሉጌታ፤ የበጎ ፈቃደኞቹ አገልግሎት ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል የላቀ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ። 

ይህን ሃሳብ የሚጋሩት ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህይወት ሰለሞን፤ “በጎ ፈቃደኞቹ ለከተማዋ እየሰጡት ያለውን ግልጋሎት የሚመጥን ምስጋና እያገኙ አይደለም” ይላሉ።

 

በጎ ፈቃደኞቹ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት እየሰሩት ባለው ስራ በተለይ ሴቶችን ኢላማ ያደረጉ የስርቆት ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውንም አመላክተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ኃላፊ ሚደቅሳ ከበደ፤ በከተማዋ የፀጥታ ማስጠበቅ ሂደት በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በስራ ላይ መሆናቸውን ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል። 

“ከዚህ ውስጥ የሰላም ሠራዊት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል” የሚሉት ኃላፊው፤ ማህበረሰቡን በሰላም ሠራዊት በማደራጀት በነጻ አገልግሎት አካባቢን የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

የበጎ ፈቃድ ስራዎች በቅድመ መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ በመደረጉ የከተማዋ የወንጀል ምጣኔ መቀነሱንም አስረድተዋል።

 

በጎ ፈቃደኞች በየጊዜው ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚደረግ እና በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 22 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። 

በቀን፣ በምሽት እና በሌሊት በሦስት ፈረቃዎች 2 ሺህ 41 የሠላም ሠራዊት አባላት በ4 ሺህ 992 ብሎኮች እየሰሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል። 

በሜሮን ንብረት


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top