ሎጎ ሀይቅ

1 Mon Ago 276
ሎጎ ሀይቅ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሁነት የተፈጠሩ እጅግ ማራኪ የሆኑ ሀይቆች መገኛ ናት።

ከነዚህ ሀይቆች መሀል በስሙ ከተማ የተሰየመለት የወሎ ሀይቅ ከተማ ውበት የሆነው የሎጎ ሀይቅ ተጠቃሽ ነው።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው ሎጎ ሀይቅ በሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበ፣ የመልክዓ ምድራዊ ገጽታው ዕይታን የሚማርክ፣ ከውቢቷ ደሴ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የቱሪስቶችን ቀልብ መያዝ የሚችል የመስህብ ሥፍራ ነው።

የሎጎ ሀይቅ ከመዲናችን አዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር 470 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘው ይህ ውብ የተፈጥሮ ሀይቅ በሱ የተነሳ ሀይቅ የተሰኘውን ስያሜ ካገኘችው ከሀይቅ ከተማ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ሀይቁ ከባህር ወለል በላይ 1 ሺህ 950 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ስፋቱ 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንና ጥልቀቱ ደግሞ ከ23 እስከ 88 ሜትር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በደቡብ ወሎ ዞን ሦስት የተለያዩ የተፈጥሮ ሀይቆች የሚገኙ ሲሆን፤ በስፋት ትልቁ ሎጎ ሀይቅ ነው። ሌሎቹ ሁለቱ የተፈጥሮ ሀይቆች አርድቦ እና ማይባር ይባላሉ። ሎጎ እና አርድቦ ሀይቆች በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኙ ሲሆን፤ ማይባር ሀይቅ ደግሞ በአልብኮ ወረዳ ይገኛል።

የሎጎ ሀይቅ በዓሣ ምርትም ይታወቃል፤ ቀረሶ፣ ዱቤና አምባዛ የሚባሉ የዓሣ ዝርያዎች በሀይቁ ውስጥ ይገኛሉ።

በሀይቁ ላይ የሞተር ጀልባዎችን ጨምሮ ለጎብኚዎች የትራንስፖርት እና የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ ጀልባዎች ያሉ ሲሆን፤ መለስተኛ ሎጆች፣ ሆቴሎችና ካፊቴሪያዎችም በአካባቢው ስለሚገኙ ለጎብኚዎች ምቹ የቱሪስት መዳረሻ ነው።

ይህ በመልክዓ ምድራዊ ገፅታው ውበትን የተላበሰው የሎጎ ሀይቅ የ"ገበታ ለትውልድ" አገራዊ ፕሮጀክት አካል ውስጥ ከተካተቱ ፕሮጀክቶች አንዱ በመሆን የመልማት ስራ ላይ ይገኛል።

በሀይቁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ በመባል የሚታወቀው የአቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም ይገኝበታል።

ይህ ገዳም ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር ቱሪስቶች የሚጎበኙት በመሆኑ የተለያዩ ቅርሶችን የያዘ ሙዚየምም ያለው ነው።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top