ማዕቀብ ሊገታው ያልቻለው የቻይና ኢኮኖሚ ግስጋሴ

3 Mons Ago 570
ማዕቀብ ሊገታው ያልቻለው የቻይና ኢኮኖሚ ግስጋሴ

አሊያንዝ ትሬድ የተባለ ተቋም ባካሄደው ጥናት እስያዊቷ ቻይና የዓለማችን የንግድ ፊታውራሪ መሆኗን እያስመሰከረች መሆኑን ይፋ አድርጓል። ዓለም አቀፍ ኢንሹራንስ አቅራቢ ኩባንያ የሆነው አሊያንዝ እንደሚለው፥ አሁን ቻይና በደረሰችበት ሁኔታ ካለቻይና መቆም የማይታሰብ እየሆነ ነው። 

ይህ የቻይና ተፅዕኖ ደግሞ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የንግድ ውድድር ላይ ከፍተኛ እየሆነ አብዛኛዎቹ ታላላቅ የምዕራባውያን የንግድ ኩባንያዎች ከኋላ ለመከተል እየተገደዱ እንደሆነ በጥናት ተደግፎ ቀርቧል። 

ከቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ስፔይን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የተውጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ኩባንያዎች በዚህ የዳሰሳ ጥናት የተካተቱ መሆኑን ነው አሊያንዝ የሚገልጸው። 

ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይ በቻይና ወጪ እቃዎች ላይ ያላቸው የጥገኝነት ደረጃ የተለያየ ቢሆንም፤ እነዚህ ሀገራት በአማካይ 50 በመቶ የገቢ ምርታቸው በቻይና ላይ ጥገኛ የሆነ ነው። በነዚህ ሀገራት የሚገኙ ኩባንያዎች ከቻይና አቻዎቻቸው ተወዳድረው ከማሸነፍ ይልቅ የእነርሱን እግር መከተልን እንደምርጫ ለማድረግ መገደዳቸውንም ነው ጥናቱ የሚያመላክተው። 

ጥናቱ እንደሚለው፥ በጀርመን እና በስፔን ከሚገኙ ኩባንያዎች 39 በመቶ፤ እንዲሁም በፈረንሳይ ከሚገኙ ኩባንያዎች ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት የቻይና ኩባንያዎችን ፈለግ መከተል ይፈልጋሉ። እንዲህ ያሉ ኩባንያዎች በከፍተኛ ደረጃ የዓለምን ምጣኔ ሀብት ተቆጣጥራለች በምትባለው አሜሪካ ውስጥ እንኳን 27 በመቶ ይሆናሉ። በዚህ ሁኔታ የአውሮፓ ኩባንያዎች ከአሜሪካኖቹ ጋር ሲነጻጸሩ ብዙ እየተጨነቁበት እንዳልሆነም ነው መረጃው የሚያመላክተው። 

የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ፕሮግራም ከፍተኛ የምርምር ባለሙያ የሆኑት ማይክል ክላይን ይህን ሀሳብ አይቀበሉትም። በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ለሚሠራው ቻታም ሀውስ (Chatham House) እንደጻፉት፥ የቻይና ኢኮኖሚ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን እየጎተተው ነው። ለዚህ ሀሳባቸው የሚያቀርቡት መከራከሪያም፥ በዘመናዊው ዓለም ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚባለው 'ከፍተኛ ጥራት ያለው ዕድገት' እንጂ ‘ፈጣን ዕድገት’ እይደለም የሚል ነው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፥ እንደ ሪልስቴት ያሉ እሴቶች ዋጋ በጣም እየወረደ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ በጣም እየቀነሰ እና የዋጋ ግሽበት እየተባባሰ ባለባት ቻይና፤ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ለዓለም አቀፉ ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረገ አይደለም። 

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ "ንግድን ማዛባት" ብለው የሚጠሩትን የቻይናን የንግድ ግስጋሴ በመቀልበስ ከቤጂንግ ጥገኝነት ለመላቀቅ የተለየ ስትራቴጂ ለመከተል ቢሞክሩም እየተሳካላቸው አይደለም። 

ቻይና፥ ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ፀረ-ቻይና ፖሊሲዎችን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን ለማደናቀፍ እየሠሩ ነው ትላለች፤ በዚህም በጉልበት ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው በማለት ትገልጻለች። 

ምዕራባውያኑ በግንቦት ወር ጃፓን በተደረገው የቡድን 7 የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቤጂንግን "ዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ ለማዛባት እየሞከረች ነው" የሚል ወቀሳ አቅርበዋል። ይህን አካሄዷን ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ መከተል አለብን ሲሉ፤ ቻይና በአንጻሩ ክሱን ውድቅ አድርጋ "ምዕራባውያኑ በቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብ ተቸክለው የቀሩ ናቸው" ብላቸዋለች። 

ይህ የቻይና ግስጋሴ ያሰጋት አሜሪካ ታዲያ በቻይና እቃዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ጉዞዋን ለመግታት እየታተረች ትገኛለች። ይህም 18 ቢሊዮን በሚያወጡ የቻይና የወጪ ምርቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ነው የተገመተው። 

ቻይና በኤሌክትሪክ መኪናዎች ዘርፍ እየተጓዘችበት ያለው ፍጥነት አሜሪካን ስጋት ላይ የጣላት ሲሆን፣ ይህን ለመግታት በየጊዜው ከፍተኛ ታሪፍ ብትጥልም ያሰበችውን ያክል የተሳካላት አይመስልም። የቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በዋጋም፣ በጥራትም ተጠቃሚን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸው፣ ለአሜሪካ ራስ ምታት እንደሆነባት ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልጹት። 

በቅርቡ ቻይናን የጎበኙት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቻይና የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ከአሜሪካ በጣም የተሻሉ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። ፑቲን ሁኔታውን ሲገልጹም፣ "በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ ዓለም እየሄደበት ያለው መንገድ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን እያሰፈነ ነው፤ አሜሪካ በቅርቡ በቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችው ከፍተኛ ታሪፍ ከፍትሃዊ የገበያ ውድድር ፍርሃት የተነሳ ነው" ብለዋል። 

የቴስላ መሥራች እና ባለቤት የሆነው ቱጃሩ ኤለን መስክም ቢሆን አሜሪካ በቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የምትጥለው ታሪፍ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር ላይ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ፣ ዘርፉን እንደሚጎዳ በመግለፅ ተቃውሟል። 

እትላንቲክ ካውንስል ላይ የሰፈረ አንድ ጥናት እንሚያመለክተው፥ ቻይና ለሚጣሉባት ማዕቀቦች እና የቡድን 7 ጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች ትገኛለች። ተገዳዳሪ ዕድገቷን ተከትሎ ሊመጣባት የሚችለውን የምታውቀው ቻይና፣ ትልልቅ ኩባንያዎቿ በመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው በማድረግ፣ ከፋይናንስ ሥራዎች ይልቅ በሜጋ ፕሮጀክቶች ኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍ፣ ለሌሎች ጫናዎች አጸፋ ምላሽ ከመስጠት በመቆጠብ፣ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ላይ በማተኮር እና ራሷን ከዶላር ተፅዕኖ በማላቀቅ፣ ጫናዎቹን ለመቋቋም እየሠራች እና እየተሳካላት እንደሆነ ጥናቱ ያመላክታል። 

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ እንደ አሜሪካ በቻይና የገቢ እቃዎች እና ኩባንያዎች ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ የተለሳለሰ አቋም መያዙን ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። በተለይም የቡድን 7 አባል ሀገራት አሁንም ቻይናን ለወጪ ምርቶቻቸው መዳረሻ አድርገው ስለሚመለከቷት፣ የአሜሪካን መንገድ እንደማይከተሉ የአትላንቲክ ካውንስል ጥናት ያሳያል። 

በሌላ በኩል የቻይና የገበያ ጥናት ምርቶቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ይነገራል። ቻይና የምታመርታቸው ምርቶች ደረጃ የገዢዎቹን አቅም ከግምት ያስገባ መሆኑ ምዕራባውያንን የፈተነ ሌላ የግስጋሴዋ ምስጢር እንደሆነ የኢኮኖሚ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top