የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነቶች ተጠንተው መሰነዳቸው፣ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ለማጽናት ወሳኝ ሚና አለው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

3 Mons Ago 540
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነቶች ተጠንተው መሰነዳቸው፣ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ለማጽናት ወሳኝ ሚና አለው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

 

የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ አመራሮች በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ (ፕሮፋይል) ጥናት ፕሮጀክት ላይ ተወያይተዋል። 

የውይይት መድረኩን የመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለብዙ ዘመናት እንደ ድር እና ማግ ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች መሆናቸውን አውስተዋል። 

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀገር ባለቤቶች እንዲሆኑና በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚሰራ ገልጸው፤ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነቶች ተጠንተው መሰነዳቸው የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ለማጽናት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እነማን ናቸው? በየት አካባቢ ነው የሚኖሩት? ብዛታቸው፣ ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ምን ይመስላል? የሚለውን ማጥናትና ለትውልድ ማስተላለፍ መጥበብ ሳይሆን ያሉበትን ሁኔታ በትክክል አውቆ የሚገባቸውን ጥበቃ ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል አፈ ጉባኤው። 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ (ፕሮፋይል) ጥናት እንዲጀመር እቅዱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጸድቆ ሥራው ብዙ ጊዜ ሲጀመርና ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ሲቋረጥ መቆየቱትን አቶ አገኘሁ አንስተዋል። 

ጥናቱ በሕዝቦች መካከል ያለው መከባበርና አንድነት እንዲጠናከር ያግዛል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት መገለጫ የሆኑት ነባር ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮችና እምነቶች ተጠንተው እንዲሰነዱ አሳስበዋል። 

በውይይት መድረኩ፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ፥ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ (ፕሮፋይል) ጥናት አነሳሽ ምክንያቶች፣ ጥናቱን ለማስጀመር የነበረውን ውጣ ውረድ እና ጥናቱ ተጠናቆ ተግባራዊ ሲሆን ለሀገር የሚያበረክተውን ፋይዳ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ማኅበራዊ ጥናት ተማራማሪ የሆኑት ዶ/ር ባይለየኝ ጣሰው በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን ማጥናትና ማወቅ የምንችልበት ዕድል ካለ በሚል የጥናት ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ አስታውሰው፤ ሀገራችንን ከልባችን የምንወዳት ከሆነ እንወቃት፤ ሀገራችንን እና ራሳችንን ካወቅን የምናደርገውን እናውቃለን፤ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን በድፍረት እንደጀመርነው ሁሉ፣ ይህን ፕሮጀክት በድፍረት መጀመራችን ሀገራችንን ለማወቅ የሚያስችለንን ዕድል ያሰፋልናል ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ ለሕግ አውጪዎችና ለፖሊሲ አመንጪዎች ያለውን ጠቀሜታ ዘርዝረው፤ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊ፣ ተመጣጣኝና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲፋጠን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ መጠቆማቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top